
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በ76ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በኒዮርክ ንግግር አድርገዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆች የጋራ ተጠቃሚነት እና በሀገራት ሉዓላዊነት ውስጥ ጣልቃ የማይገባ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ሀገሬ ከሶስት ዓመታት በፊት ለውጥ በማድረግ ለዴሞክራሲ፣ ለሰው ልማት፣ ሰብዓዊ መብት እና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፍላጎቶች ላላቸው ቡድኖች የውይይት እና የአንድነት በር እንዲከፈት አድርጋለች ብለዋል፡፡
በዚህም አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን ሪፎርሙ ያለፈተና አልተከናወነም ሲሉ ለጉባዔተኛው አብራርተዋል፡፡
በዚህ ሂደት ጥቅሜ ተነካብኝ ያለው ወንጀለኛው ቡድን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንን ከጀርባው ካጠቃው እና በርካታ ጥፋት ካጠፋ በኋል መንግስት ህግን ለማስከበር እና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ እርምጃ ወስዷል፡፡
መንግስት የሰብአዊ ድጋፍ ሲያደረግ ቡድኑ ድጋፉ እንዲደናቀፍ እና የዜጎች ስቃይ እንዲበረታ አደርጓል፡፡ በውሸት ፕሮፖጋንዳ የተካነው ቡድን በርካታ አፍራሽ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡ የውሸት ክስተቶችን አስተጋብቷል፤ ቀድሞ በተዘጋጅ ስም የመጣፋት ዝንባሌ ከፍተኛ ዘመቻ አድርጓል፡፡
ሕዝባችን ካለበት ችግር አንጻር በቂ ነው ባይባለም መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ መንግስታዊ ግዴታውን ለመወጣት በመስራት እና የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲመረመሩ እንዲሁም እርምጃዎች እንዲወሰዱ አደርጓል ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡
የጥፋት ቡድኑ በሚከፍላቸው የፕሮፖጋንዳ ሚዲያዎች አማክኝነት እና በተሳሳተ የፖሊሲ አተያይ የውጭ ፖሊሲ መርህ ሲጣስ ተስተውሏል ያሉት አቶ ደመቀ መርሆች መከበርም አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከወዳጆቻችን የሚመጣውን ገንቢ ምክረ ሀሳብ በመልካም ጎኑ የምንመለከተው ሲሆን፣ አሁን የገጠምን ፈተና ከኢትዮጵያ አቅም በላይ አይደለም፡፡ በጥፋት ቡድኑ ላይ ኢትዮጵያ የጀመረቸውን እርምጃ መደገፍ የቀጠናውን ሰላም መደገፍ ነው ሲሉ አቶ ደመቀ አስምረው ተናግረዋል፡፡
በየትኛውም መልኩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባን ኀይል ኢትዮጵያ አትታገሰም ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡
ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት ያላት ሲሆን ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር አለመግባባት በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ናት ነው ያሉት፡፡
የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት የትውልድ ጥያቄን ምላሽ የያዘ እና ከወንዙ ተጠቃሚ ሀገራት ጋር የጀመርነውን ድርድር መርህን ተከትለን ውይይት የምናደረግ ሲሆን ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጽኑ አቋም አለን ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡ ነገር ግን የኀይል ማመንጫ ፕሮጀክታችን በቅኝ ግዛት ሌጋሲ እና ጠቅላይነት አይቆምም በማለት አስገንዝበዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m