የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉን አቀፍ ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።

407

መስከረም 15/2014 ዓ.ም(አሚኮ) ነገ የሚከበረው የመሰቀል ደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ ይውል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉን አቀፍ ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።

ቤተክርስቲያኗ ያስተላለፈችው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

የሰላም፣ የአንድነት፣የፍቅርና የስምምነት መገለጫ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በነገው ዕለት በመላ ኢትዮጵያ ተከብሮ የሚውል ሲሆን በዓላችንን በሰላምና በደስታ ማክበር እንችል ዘንድ ከጸጥታ ማስከበር ጋር ተያይዞ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚተላለፉ መልዕክቶችን መከታተልና መተግበር እንደሚገባ ቤተክርስቲያናችን ትገልጻለች። በተለይም ወደ መስቀል አደባባይ የሚጓዙ ምዕመናን የጸጥታ አካላት ለሚያደርጉት ፍተሻ ፍጹም ተባባሪ በመሆን ግብረ ሽበራን መከላከልና አጠራጣሪ የሆኑ ምልክቶችንም ሲያጋጥመው ለጸጥታ አካላት በመጠቆም በዓላችንን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ማክበር እንችል ዘንድ ክርስቲያናዊ ጨዋነትን የተላበሰ ትብብርና ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪዋን አቅርባለች።

በበዓሉ ወቅት በሚደረጉ ትርኢቶች፣ መንፈሳዊ ዝግጅቶችና በዓሉን ለማክበር በመስቀል አደባባይ የሚገኙ ምዕመናን ሁሉ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ሕግና ሥርዓት አክባሪዎች መሆናችንን በሚያስመሰክር መልኩ ሕጋዊውንና በሕገ መንግሥቱ የጸደቀውን ሰንደቅ ዓላማ ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አርማ ያለበት ያልተጣጣፈና በግልጽ ከፊትም ከኋላም የሚታይ ባንዲራ ብቻ ይዞ መውጣትና ከዚህ ውጪ ያሉ ማንኛቸውንም አርማና ባንዲራዎችን ባለመያዝ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ቤተክርስቲያናችን ለማሳሰብ ትወዳለች።

በዓሉ በምልዓተ ሕዝብ የሚከበር በዓል ከመሆኑ አንጻርም ሁሉንም የኮቪድ ፲ ፱ የቅድመ ጥንቃቄ መርሆችን በማክበርና በመፈጸምም የራሳችንንና የወገኖቻችንን ህይወት መጠበቅ እንደሚገባንም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በበዓሉ ወቅት በመስቀል አደባባይ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኮቪድ ፲ ፱ ምርመራና ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አውቃችሁ ምርመራ በማድረግና ክትባት በመከተብ የበሽታውን ሥርጭት በጋራ እንድንከላከል በሚኒስቴር መሥሪያቤቱ አማካኝነት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እንወዳለን።

“ልዑል እግዚአብሔር በዓላችንን የሰላም፣የደስታ ፣የፍቅር ፣የአንድነትና የስምምነት ያድርግልን” ስትል ቤተክርስቲያኗ ጥሪዋን አስተላልፋለች።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleበየትኛውም መልኩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባን ኀይል ኢትዮጵያ አትታገሰም” አቶ ደመቀ መኮንን