❝አሸባሪው የትህነግ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የአማራ ወጣቶችን በግዳጅ ግንባር ለማሰለፍ እየሠራ ነው❞ የዓይን እማኞች

239
መስከረም 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ የቆየችው በገዥዎች ኀይል ብቻ ሳይኾን በሕዝቦች መካከል ያለው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በፈጠረው ጠንካራ መስተጋብር ነው። ዘውግና ሃይማኖትን የተሻገረው ማኅበራዊ ትስስር ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንድትቀጥል አድርጓታል።
ይሁን እንጂ በበታችነት ህመም የተለከፈው አሸባሪው ትህነግ ባለፉት አርባ ዓመታት በዘራው የጥላቻ መርዝ የሕዝቦችን አብሮነት እና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲሸረሸር ሠርቷል።
በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያውያን ግብረገባዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ፈጽሟል። ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለዋል፤ ሀብት እና ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ወድሟል። አሁን ላይም ይህ ኢሰብዓዊ ድርጊት በሽብር ቡድኑ በይፋ ተባብሶ መቀጠሉን በሳምንቱ ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ደሴ የገቡ እማኞች ነግረውናል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ አካባቢውን ከወረረ ጊዜ ጀምሮ የፈጸማቸው ድርጊቶች የውጭ ባዕድ ወራሪ እንኳን ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በዚህም ከሰብዓዊነት በታች በመውረድ ወጣቶችን፣ እናቶችንና አረጋውያንን ገድሏል። አስከሬን እንዳይነሳ በመከልከል በጅብ እንዲበላ አድርጓል ብለዋል።
የንግድ ተቋማትን፣ የመኖሪያ ቤቶችን እና የመንግሥት ተቋማትን ዘርፏል። በአሸባሪው ቡድን በደረሠ ዘረፋና ውድመት የህክምና ተቋማት አገልግሎት በመቋረጡ ተመላላሽ ታካሚዎች ህይወታቸው እያለፈ መኾኑንም ገልጸውልናል። ማኅበረሰቡም ለርሃብ መጋለጡን አንስተዋል።
የሽብር ቡድኑ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት በማድረሱ ችግሩ አሁን ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ባመረተው ሰብል እና ባረባቸው እንስሳት ማዘዝ ባለመቻሉ ከዶሮ ጀምሮ በግ፣ ፍየል እንዲሁም በሬዎቹ በሽብር ቡድኑ እየታረዱ ነው፤ ወጣቶች በቀያቸው በነጻነት መንቀሳቀስ አይችሉም። አሁን ደግሞ አሸባሪው ትህነግ ይባስ ብሎ ወጣቶችን አስገድዶ ግንባር በማሰለፍ የጥይት እራት ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገልጸውልናል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከዚህ የአሸባሪ ቡድን ሴራ ለማትረፍ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በሽሽት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የዓይን እማኞች ተፈናቃዮች ከዚህ ወራሪ ቡድን ነጻ ለመውጣት በሚደረገው ትግል ሁሉም በሚችለው ሁሉ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
አሸባሪው ትህነግ እየፈጸመ ያለውን ግፍ ለማስቆምና ቡድኑን ለመቅበር በአንድነት መታገል ከሁሉም የሚጠበቅና ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው አሸባሪው የትህነግ ቡድን በደብረታቦር ከተማ ፈጽሞት በነበረው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።