
ደብረታቦር፡ መስከረም 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው እና የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የተጎዱ ወገኖችን በደብረታቦር ከተማ ተገኝተው አጽናንተዋል።
ባለሀብቱ ለተጎዱ ወገኖችም ድጋፍ አድርገዋል።
ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ማንኛውም ባለሀብት በተናጠልም ይሆን በጋራ በመሆን የተጎዱ ዜጎችን መደገፍ ይጠበቅበታል ብለዋል። ድጋፍ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ወደራሳችን በማቅረብ ልናጽናናቸው ይገባል ነው ያሉት።
በሽብር ቡድኑ የተጎዱ ዜጎችን የተመለከተ ጥናት ከተከናወነ በኋላ በግልም ሆነ በጋራ ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ባለሀብቱ ጠቁመዋል።
ሁሉም ባለሀብት በተደራጀ መልኩ የተጎዱ ወገኖችን በቋሚነት ሕይወታቸውን የሚቀይር ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ጥሪ አድርገዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም በደብረታቦር ከተማ ባስወነጨፈው ከባድ መሳሪያ ጥቃት 5 ቤተሰቦቻቸውን ያጡት አቶ ድረስ ነጋ በባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው የ500 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም አቶ ድረስ አመስግነዋል።
አቶ ወርቁ በሽብር ቡድኑ ከባድ መሳሪያ ቤታቸው የወደመባቸው የአቶ እንየው ዳኛው ቤትን በመመልከት የ 300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል። አቶ እንየው የተደረገላቸው ድጋፍ ቤታቸውን ለመጠገን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ