
አዲስ አበባ፡ መስከረም 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በውይይታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በአማራ አና በአፋር ክልሎች እርዳታ በሚያደርሱባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በኒዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 76ኛው መደበኛ ሰብስባ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከመደበኛ ስብሰባዎች በተጨማሪ ስኬታማ የጎንዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራው የልዑካን ቡድን ከጋቦን፣ ከኬንያ፣ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ፣ ከአየርላንድ፣ ከኖርዌ፤ ከዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን ከዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ደግሞ ከተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ፤ ከዓለማቀፍ የምግብ ፕሮግራም አንዲሁም ከቀይ መስቀል ማኅበር ኀላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ እውነታዎች ዙሪያ ማብራሪያ መሰጠቱን ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ከኒዮርክ በስልክ ለአሚኮ አስረድተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት ኬንያ በጸጥታው ምክር ቤት ላይ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ተለዋጭ አባል ከምትሆነው የጋቦን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ቆይታም ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ድጋፍ ዙሪያ መምከራቸውን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተራድኦ ድርጅት ኀላፊዎች ጋር በመወያየት ፍትሐዊ ድጋፍ አንዲያደርጉ መምከራቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ባደረጉት ውይይት ፍትሐዊ እርዳታ እንዲኖር እና አሸባሪው ቡድን በወረራቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎች እርዳታቸውን እንዲያደርሱ መገለጹን ነግረውናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ሊረዱት ያልፈለጉ ወይም ያልተረዱ እንደ አየርላንድ አና መሰል ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በመወያየት የተሻለ ግንዛቤ መስጠት እንደተቻለ በማብራራት የልዑኩ ጉዞ በእስካሁኑ ቆይታው ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m