
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት የሕይዎት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ፈተና የተዳረገችው የኢትዮጵያን መኖር የማይሹ የውጭ ኃይሎችን ሴራ በተቀበሉ ጥቂት ግለሰቦች እጅ መውደቋ ነበር ብለዋል፡፡
በዘመናት መካከል በተለያዩ መስኮች ለሀገር ከሠሩ ሰዎች አንዱ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ፈጣን ተማሪ፣ ጀግና ወታደር እና ቆፍጣና የጦር መሪም እንደሆኑ ግለ ታሪካቸው ያመላክታል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የገንጣይ አስገንጣይ ኃይሎች ብቅ ብቅ ሲሉ፣ ጊዜ እና የውጭ ኃይሎች ድጋፍ አቅም ሲሰጣቸው “ኢትዮጵያ” ከሚለው ጠንካራ አቋማቸው ዝንፍ ያላሉት የጦር መሪ ረጅም ዘመናቸውን በእስር እንዲያሳልፉም አስገድዷቸዋል ይባላል፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ፡፡
ኢትዮጵያ የእምነት ምድር፣ የጀግኖች ሀገር፣ የብሔር ሰብጥር፣ ቱባ ባህል እና እሴት ያላት ሀገር ናት ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ በልጆቿ መስዋእትነት ተከብሮ የኖረው ነፃነቷ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶቿ ፈተና አብዝተውባታል ብለዋል፡፡
ፈጣሪን የሚፈሩ እና ሞትን የሚደፍሩ ልጆች ያሏት ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የበቀለባትን ሰንኮፍ ሁሉ በመንቀል ትልቅ ሀገር አስረክበውናልም ብለዋል፡፡
ምዕራባውያን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ድሮም የኢትዮጵያ በጎ አሳቢዎች አልነበሩም የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ይዘው እንዳይዘውሩ የነፃነት ቀንዲል ሰለሆነችባቸው አምርረው ይጠሏታል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገጠማት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትም ምክንያቱ ጠንካራ እምነቷ እና አልንበረከክም ባይነቷ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ እንዳለፈው ዘመን የመንግሥት አስተዳደር የከፋ ዘመን ገጥሟት ያውቃል ብዬ አላስብም የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ከዘረኝነት፣ ከራስ ወዳድነት እና ስንፍና ወጥተን አሁን በታየው የሀገራዊ አንድነት መስመር ዳግም ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ኃይሎች እጅ ጥምዘዛ እና ጫና ለጊዜው ፈታኝ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በአንድ ከቆሙ የማያልፉት ፈተና እና የማይሻገሩት መከራ አይኖርም ነው ያሉት፡፡
ብርጋዴር ጀኔራል ካሳየ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ጠንካራ ሀገራዊ ፍቅር እና ጥብቅ ወታደራዊ ሞራል ያለው የመከላከያ ኃይል የምትገነባበት ጊዜ መሆኑን ጠቁመው “ውድ ሕይዎቱን ለሀገሩ የሚሰጥ ሁሉ ክቡር ነው” ሕዝቡም ለወታደር እና ውትድርና ሙያ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያርም መሥራት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡ በተለይም የተማሩ ወጣቶች በውትድርና ሙያ መስክ የመኮንንነት ስልጠናዎችን እየወሰዱ ምጡቅ የመከላከያ ኃይል መፍጠር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
