በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ለተፈናቀሉ ወገኖች 500 ሺህ የሚገመት የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡

175
ደባርቅ: መስከረም 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፎረሙ በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ከሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች 500 ሺህ የሚገመት 100 ኩንታል ፍርኖ ዱቄት ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡
ድጋፉን የፎረሙ የሥራ ኀላፊዎችና አባላት በቦታው ተገኝተው አስረክበዋል፡፡
ድጋፉን ካስረከቡት መካከል የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ኀላፊ ዶክተር አስማረ ደጀን አሸባሪው የትህነግ ቡድን አማራን ለማጥፋት ለዓመታት ሠርቷል፡፡ አሁን ላይ በንጹሐን ሰዎች ላይ እየፈፀመ ያለው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለዓመታት አማራን ለማጥፋት የሠራው ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አስማረ እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ አማራን ለማጥፋት አሁንም እየሠራ ስለመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉ የጥፋት ተግባሮች ማሳያ ናቸው። ይህንን አሸባሪ ቡድን ማጥፋት ይገባል፤ ትህነግ ካልጠፋ አማራ እንደ ሕዝብ መኖር አይቻለውም ነው ያሉት፡፡
አሸባሪውን ትህነግ ለማጥፋት በሚከናወኑ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፎረሙ አባል ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በጦርነቱ ተጎጂ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመለዬት፣ የጉዳት መጠኑን በማጥናትና በመተንተን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማሳወቅ እና ማኅበረሰቡ ወደቀደመ ህይወቱ እንዲመለስ የማድረግ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በአሸባሪው ቡድን የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ በለጠ ጥላዬ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች በማከፋፈልና በየወረዳው በየቤታቸው ለሚገኙና ሀብት ንብረታቸው ለተዘረፈባቸው ወገኖች በማድረስ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየደምበጫ ዙሪያ ወረዳ በማይጠብሪ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦርና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
Next articleባለሀብቱ ወርቁ አይተነው በማይጠብሪ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦርና ለተፈናቀሉ ወገኖች 25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ ።