
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ የስራ ቆይታቸው ጎን ለጎን ከተመድ ምክትል ዋና ሐጸፊ አሚና ጄኔ መሐመድ ጋር ተወያይተዋል።
በዘላቂ ልማት ግቦች አፈፃፀም፣ በሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ አሰጣጥ እና ወቅታዊ የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን በተመለከተ በዝርዝር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግስት በመልሶ ማቋቋም እና በመልሶ ማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሂደት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በላቀ አጋርነት ከተመድ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።
“በአሁን ጊዜ ሀገራችንን እየገጠሟት ካሉት የፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ማልማት ተልዕኮን ለማስፈፀም በተመድ በኩል የበለጠ ትብብር እና ድጋፍ እንጠብቃለን” ብለዋል አቶ ደመቀ።
በመጨረሻም እስካሁን ድረስ የተመድ በልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋፅዖ በማመስገን፤ በአሁን ጊዜ ወቅቱ የተሻለ ትብብርና መደጋገፍ እንደሚጠይቅ አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል ሲል የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ