
❝በእነርሱ ህልፈት እኛ ቆመን ለመናገር በቅተናል፤ ወደፊትም ሞቱብን ብለን ጠላትን ለማጥፋት ከምናደርገው ትግል ወደ ኋላ አንልም❞ በጀግንነት ከጠላት ጋር ሲዋደቁ የተሰው የሰማእታት ቤተሰቦች
መስከረም 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊት እናት ጀግና ትወልዳለች፣ አጀግና ታሳድጋለች፣ ትወልዳለች፣ አፈር በበላሁ እያለች ታበላለች፣ ታጠጣለች፣ ሀገር ሲነካ ደግሞ እምብኝ ብላ ትነሳለች፣ መቀነቷን ታጠብቃለች፣ ነፍጥ ታነሳለች፣ የጠላትን ግንባር መትታ፣ በመጣበት ታስቀራለች፣ ሀገርና ወገን ነፃ ታደርጋለች፣ ኮርታ ታኮራለች።
ለሀገር ሲታገል ልጇ ቢሰዋ የእናትነት አንጀት እየታገላት፣ ያሳደገ ልብ አልቆርጥ እያላት፣ እንባ ቢታገላት ሐዘኗን ገታ አድርጋ የልጇን ደመኛ ልትታገለው፣ በመጣበት ልታስቀረው ትገሰግሳለች። ሳይሰስት የወደደው አንጀቷ፣ ላይምር ይጠላል፣ እንስፍስፉ የእናትነት ስሜቷ ላይበርድ ይግላል፣ እስከመጨረሻው ይታገላል።
ጠላትን ከምድረ ገፅ ነቃቅሎ ይጥላል። ኢትዮጵያውያን በሀገር ሲመጡባቸው ሐዘን አያስቆማቸውም፣ መከራ አይበግራቸውም፣ ከብረት እየጠነከሩ፣ በአንድነት ስለ ሀገር ፍቅር እየዘመሩ ይወድቃሉ እንጂ።
አሸባሪው ትህነግ በስሜን ጎንደር ዞን ዳባትና ደባርቅን ቆርጦ ለመያዝ ባደረገው ሙከራ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ መደምሰሱን መዘገባችን ይታወሳል።
አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ በተደረገው ትግልም የአካባቢው ማኅበረሰብ የፈፀመው ጀብድ አስደናቂ ነበር። በዚያ ትግል ከጠላት ጋር ተናንቀው ሲዋደቁ ከተሰው ጀግኖች ቤተሰቦች ጋር ቆይታ አድርገናል።
ወይዘሮ ምግብ ጥሩነህ ይባላሉ። በተደረገው ውጊያ አክሊሉ ወረደ የተባለ ልጃቸው የጠላትን አንገት አስደፍቶ በጀግንነት ተሰውቷል። በደሙና በአጥንቱ ሀገር አትርፏል፣ ወገን ታድጓል። ይህም መስዋእትነቱ ብዙዎችን አኩርቷል። እናቱ ወይዘሮ ምግብም በልጃቸው ጀግንነት ኮርተዋል። ❝ልጄን ሳሳድገው ቆስጣ ሽጬ ነው፣ ልጄ በመሞቱ ባዝንም አንጀቴ ቢንቀጠቀጥም እንኳን ሕዝቤ አልታረደ፣ እንኳን ሀገሬ ዳባት አልተደፈረች። የሚለውን ቃሌን መቼም አላጥፈውም❞ ነው ያሉት።
በልጃቸው መስዋእትነት እናት ቢያዝኑም በሠራው ጀብዱና ሀገር በማትረፉ ኮርተዋል፤ ተመክተዋልም። ❝ልጄ ገስግሶ የሄደው አባቱ መሣሪያ እየሰጠ፣ እያስወለወለ፣ እያስገጠመ ስላሳየው ነው። አባቱ ዘጠኝ ወር በጋ ሙሉ፣ ወንበዴው መጣ ሲባል በየቦታው እየዘመተ መኖሩን ሀገር ያውቃል። አባቱ በጠገዴ ገብቶ እየተዋጋ ልጁም ሄዶ ነው ከጠላት ምሽግ የተገኘው። ልጄ ክላሽ ማርኳል። ከጠላት ጋር በጀግንነት ተዋድቆ ተሰውቷል❞ ብለውናል።
ወይዘሮ ምግብ ካለፈው ይልቅ ወደፊት ስለሚሠራ ጀግንነት በደንብ ማሰብ እንደሚገባም ገልጸዋል። ❝ለወደፊት ወረዳው፣ ቀበሌው፣ ፖሊሱ ይጠንክር፣ ሕዝቡን አንድ እናድርገው፣ መከራ ላለማዬት ጥቁር ልብሳችንን አውልቀን ለሚፈለገው ነገር ሁሉ ለመስዋእትነት መሄድ አለብን። መቀጠል አለብን፣ ሀገሪቱን ዳሯን አስጠብቆ ነው መቀመጥ❞ ብለዋል።
ወይዘሮ ምግብ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ሕዝብን እያዳመጡ ለሀገርና ለወገን እንዲሠሩ ጠይቀዋል። ሕዝቡን በማደራጀት ማወያየት እና ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። ለሀገር፣ ለሃይማኖትና ለወገን መዋደቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ታላቅ ወንድማቸውን ያጡት አቶ ምትኩ ሙሐባው የወንድሞቻችን ህይወት በማለፉ እንደ ቤተሰብ ብናዝንም የሞቱት ለሀገርና ለሕዝብ በመሆኑ ኮርተናል ብለዋል። ❝እነርሱ ሞተው እኛን አድነውናል፣ ሞቱ ልንላቸው አንችልም። ሁልጊዜ ኮርተን ቀና ብለን እንኖራለን❞ ነው ያሉት።
በ1990ዎቹ ወንድማቸው ለሀገር ጥሪ ዘምተው በጾረና ግንባር በጀግንነት እንደተሰው ያስታወሱት አቶ ምትኩ አሁን ለሌላ ሀገራዊ ጥሪ ወንድሜ ለሀገር ሲል ተሰውቷል ነው ያሉት። ወንድማቸው ሀገሬን አላስደፍርም በማለት በራሳቸው ትጥቅ ዘምተው ጠላትን ድባቅ መትተው በክብር መሰዋታቸውን ገልጸዋል።
ወንድሜና ሌሎቹ ጓደኞቹ ከተሰውበት ቦታ የጠላት ሬሳ ረፍርፈውት ነው የሞቱት። የጠላት ኃይል ዘር እንዳይኖር፣ ሀገር ለማጥፋት የመጣ ስለነበር፣ በእነርሱ ሞት እኛ ቆመን ለመናገር በቅተናል። ወደፊትም እኛ ሞቱብን ብለን አንቆምም❞ ነው ያሉት።
ባለቤታቸው በጀግንነት የተሰዋባቸው ወይዘሮ ፋሲካ ባዬ ❝ ባለቤቴ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለሀገር የቆመ ነው፣ ልጄን ቤተቦቼን ንብረቴን ሳይል አራት ጊዜ የዘመተ ነው። ሀገሬን ቁጭ ብዬ አላስደፍርም የሚል ጀግና ነበር። እኔ እያለሁ ልጆቼ የጠላትን ክፋት አያዩም፣ ከጠላት ጋር እጋደላለሁ እንጂ የሚል ሰው ነበር። በጀግንነቱ እንኮራለን❞ ብለዋል።
ልጃቸው በጀግንነት የተሰዋባቸው አቶ ምስጋናው መንበሩ ሀገሬን አላስደፍርም በማለት በጀግንነት መዋደቁን ተናግረዋል። ጠላትን ድባቅ መትቶ መሰዋቱን ገልጸዋል። እኛም ወደ ግንባር ሄደን ሕዝባችንና ሀገራችን ማዳን አለብን፣ እንዘጋጅ፣ ልጄ ሞቷል አልልም፣ ካሉት ልጆቼ ጋር ወደ ግንባር እሄዳለሁ ነው ያሉት። ሁሉም ይዘጋጅ፣ በጀግንነት እንቀጥል፣ እንደምናሸንፍ አንጠራጠርም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ