በ2014 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ኮሚሽኑ አስታወቀ።

257
ባሕርዳር፡ መስከረም 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በተገኘ መረጃ በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በዓመት ቢያንስ 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠር ያስፈልጋል። ኮሚሽኑ በአዋጅ ሲቋቋም ብሔራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን ለመምራት፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላትን ለማቀናጀት ለማስተባበር እንዲሁም አፈጻጸሙን ለመከታተል እና ለመደገፍ ነው። የሥራ ዕድል ፈጠራ እቅዱን ከማሳካት አኳያ እስከ 2017 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዷል። ኮሚሽኑ ባስቀመጠው መሪ እቅድም እስከ 2022 ዓ.ም 20 ሚሊዮን ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።
ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ብሔራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው። በቀረበው ሪፖርት መሰረት በ2013 በጀት ዓመት ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቶ ነበር። በዓመቱም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት እና በሌሎችም ዘርፎች ለ3 ሚሊዮን 457 ሺህ 88 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ የሴቶች ድርሻ 35 በመቶውን ይይዛል።
ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት ዓመታዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንጻር ጭማሪ ታይቶበታል፣ ከ2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የአምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው የተባለው። አማራ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሲዳማ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዕቅዳቸው በላይ የፈጸሙ ናቸው። ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ጋምቤላ እና ሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግበዋል። ቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና ሐረሪ ክልሎች ደግሞ መካከለኛ አፈጻጸም እንዳላቸው ታውቋል። በአማራ ክልል ለ892 ሺህ 291 ሰዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ክልላዊ አፈጻጸሙ 117 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን በበጀት ዓመቱ የሥራ እድል ፈጠራ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀትና በማስተባበር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ያጋጠሙ ፈተናዎች የተገነቡትን ያፈረሱ፣ የታቀደውን ወደኋላ የመለሱ በመሆናቸው በሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም አንስተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የከፈተው ጦርነት እና በርካታ ወገኖች ከውጪ ሀገራት እየተመለሱ መሆኑ በሥራ ዕድል ፈጠራው ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ተብሏል።
እንደ አቶ ንጉሱ ማብራሪያ በርካታ የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው ኢንተርፕራይዞች በጦርነቱ መውደማቸው እና የኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖ በሥራ ስምሪት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። ነገር ግን የታቀደውን በውጤታማነት ማሳካት መቻሉ ትልቅ ድል እንደሆነ ነው የተናገሩት።
በየክልሎቹ እና በፌዴራል ደረጃ የፋይናንስ እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በሥራ ስምሪት ያለውን የፋይናንስ ማነቆ በመፍታት ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል። ይሁን እንጂ በሥራ ዕድል ፈጠራ አካታችነት የሴቶች ተሳትፎ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ዝቅተኛ መሆን ቀጣይ መስተካከል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ የወደሙትን መልሶ ማቋቋም፣ ከውጪ የሚመለሱትን የሥራ ባለቤት ማድረግና በሥራ ላይ ያሉትን ቀጣይነት ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶታል። ፈተናዎችን በምናልፍበት ወቅት አዳዲስ የሥራ መስኮችን በመፍጠር ዜጎችን የሥራ ባለቤት ማድረግ የግድ ይላል ነው ያሉት።
ለዘርፉ ውጤታማነት የግል ዘርፉ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ያነሱት አቶ ንጉሱ ለዚህም መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ግዴታውን ይወጣል ብለዋል። የተጀመረው ቅንጅታዊ አሠራርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
አቶ ንጉሱ የመንግሥትና የግል ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመደጋገፍ የዜጎችን ተስፋ ለማለምለም እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። ያጋጠሙ ችግሮች ያደረሱትን ተጽዕኖ ከነ መፍትሄው የሚያመላክት ጥናት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተሠርቷል። ውይይቱም ለቀጣይ ሥራ ሁሉም የቤት ሥራውን ይዞ የሚሄድበት እንደሆነ ነው ያነሱት።
በ2014 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል። ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ወገኖች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሳይንሳዊ ጥናት መሠራቱ ተገልጿል። ባለፈው በጀት ዓመት በዘርፉ የታዩ ማነቆዎችን ለይቶ በመፍታት ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ነው የተመላከተው።
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲጠብቁ ከቦረና ወረዳ ዘመቻዉን የተቀላቀሉ የመንግሥት ሠራተኞች ጥሪ አቀረቡ፡፡
Next article❝በእነርሱ ህልፈት እኛ ቆመን ለመናገር በቅተናል፤ ወደፊትም ሞቱብን ብለን ጠላትን ለማጥፋት የምናደርገውን ትግል አናቆምም❞ በጀግንነት ከጠላት ጋር ሲዋደቁ የተሰው የሰማእታት ቤተሰቦች