
ደሴ፡ መስከረም 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ደረጀ አራጋዉ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ባለሙያ ናቸው፡፡ አቶ ደረጀ ዘራፊዉ እና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራን ለማጥፋ የፈጸመዉን ወረራ ተከትሎ በመንግሥት የቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው በወሎ ግንባር እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡
ዘማቹ የመንግሥት ሠራተኛ አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለው ጥፋት መጠነ ሰፊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህን ጥፋት በጋራ በማስቆም የሽብር ቡድኑን መቅበር አስፈላጊ በመሆኑ መዝመታቸውንም ነው ያስረዱት፡፡ የአማራ ወጣቶች ራሳቸውም ሕዝባቸውም ሰላም የሚያገኘው አሸባሪው ቡድን ሲቀበር በመሆኑ የትህነግን የሽብር ቡድን ለመቅበር መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርና ጥናት ተመርቀው በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ የነበሩት አቶ ታደለ ምስጌ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው መዝመታቸውን ነግረውናል፡፡
በተደላደለ ወንበር ላይ ሆኖ የመንግሥትን ሥራ ለማከናወን ቅድሚያ አሸባሪ ቡድኑን መቅበር አስፈላጊ በመሆኑ አሸባሪ ቡድኑን እየታገሉ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡የአማራ ወጣትም መከላከያን በመቀላቀል የወገናቸውን ጠላት መፋለም እንዳለባቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም በመካነሰላም ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ 01 ማእከል አስተባባሪ ተመስገን አንተነህ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለዉ በወሎ ግንባር አሸባሪዉን ቡድን እየደመሰሱ ይገኛሉ፡፡
አማራ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ በሚል ወረራ የፈጸመዉ አሸባሪዉ ትህንግ በወረራቸዉ አካባቢዎች በርካታ ጥፋቶችን ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ በሰዉ ልጅ ላይ መፈጸም የሌለባቸዉን ግፎች እየሠራ ያለዉን የሽብር ቡድን ለማጥፋ ዝግጁ መሆናቸዉን ገልጸዋል። ወጣቱም መከላከያን በመቀላቀል ትግሉን እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ወረራ ለአማራ የመኖር ያለመኖር የህልዉና ጉዳይ በመሆኑ የአማራ ወጣት መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ወራሪዉን ቡድን መደምሰስ እንዳለበት ዘማች የመንግሥት ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ከድር አሊ-ከወሎ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ