ከመተማ ጎንደር የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም እንዲቋረጥ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም የጠላት ቡድን የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ አስታወቀ።

193
ገንዳ ውኃ፡ መስከረም 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጽንፈኛው የቅማንት ቡድን ሴራ ምክንያት ለወራቶች ተዘግቶ የነበረው ከጎንደር መተማ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ አቶ እንዳለው ማሩ አስታውቀዋል። መንገዱ ለወራቶች ያህል በመንግሥት ሆደ ሰፊነት ሲከፈትና ሲዘጋ ቢቆይም አሁን ላይ ዞኑ ዳግም ለማዘጋት የሚንቀሳቀስና የሚተባበር ማንኛውንም የውስጥ ጠላት ለመደምሰስ በሚያስችል አቋም ላይ እንደሚገኝ ኀላፊው ተናግረዋል።
የመንገዱ መዘጋት በዞኑ ማኅበረሰብ ብቻም ሳይሆን በክልሉና በሀገር ደረጃም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ አስከትሏል ያሉት ኀላፊው የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን ማዘዣ ጣቢያውን ጭልጋ አድርጎ ሌንጫ፣ ጉባይ፣ ሽንፋና መቃ አካባቢ ሽፍቶችን በማደራጀት ንጹሃን ዜጎችን ሲዘርፍና ሲያግት፣ የልማት አውታሮችን አገልግሎት እንዳይሰጡ ሲያቋርጥ እንደ ነበር ገልጸዋል።
የሽብርተኛው ትህነግ ተላላኪና ቅጥረኛ የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን በቲሀ በኩል ሽብርተኛውን ትህነግ አስገብቶ የሽብር ተልዕኮውን ለመፈጸም ቢሞክርም በዞኑ የጸጥታ ኃይልና ማኀበረሰብ ጀግንነት መደምሰሱን ነው አቶ እንዳለው የገለጹት። መንገዱን በዘላቂነት ፍጹም ሰላማዊና አስተማማኝ ለማድረግ የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ የምዕራብ ጎንደር ዞንና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው ብለዋል ኀላፊው፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ እና የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን ከገጸ ምድር እንዲጠፋ የጸጥታ ኃይሉን በማደራጀትና ስምሪት በመስጠት የመልቀም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። መንገዱ ለኅብረተሰቡ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ጽንፈኛ ቡድኑን አሳልፎ እንዲሰጥ ከሰላም ፈላጊው ኅብረተሰብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ እንዳለው ዳግም የዘረፋና እገታ ወንጀል በሚፈጸምበት ቦታ ድርጊቱን እያየ የማያጋልጥ አካል ተጠያቂ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ሳይሰጋና ሳይሸበር ሽብርተኛው ትህነግ እና የጽንፈኛ ቡድኑ ያለበትን ቦታ ጥቆማ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ኀላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ – ከገንዳ ውኃ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው የትህነግ ቡድን በተደራጀና በባለሙያዎቹ በተደገፈ መንገድ ዘረፋና ውድመት መፈጸሙን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመላከተ፡፡
Next articleየባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ለአፋር ክልል ተፈናቃዬች ድጋፍ አደረጉ።