
ባሕር ዳር፡ መስከረም 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል ባካሄደው ወረራ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ስብራቶችን ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ነው፡፡ አሸባሪው ቡድን በወረራው ከተራ ስርቆት እስከ ተደራጀ ዘረፋ፤ ከግለሰቦች መቀነት እስከ ሙዳየ ምጽዋት በርብሮ እና ፈትሾ ያገኘውን ሁሉ ወስዷል፡፡
ድርጊቱ “የእጅ አመል” ቢመስልም ጥናቶች የሚያመለከትቱት ግን ከዚህ በተቃራኒ የተደራጀ ምዝበራ መካሄዱን ነው፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ከነሐሴ 5/2013 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም ለ9 ቀናት ባደረገው ወረራ በፈጸመው መጠነ ሰፊ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ዙሪያ ጥናት አካሂዷል፡፡
የጥናቱ አባል እና በሙያቸው ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በወረራው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና የሃብት ዘረፋና ውድመት ተፈጽሟል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን በወረራው አራት መሰረታዊ የጦር ስልቶችን እና ስትራቴጂዎችን በተጠና መልኩ መጠቀሙን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰዋል፡፡ ሽብር፣ ማጭበርበር፣ መዝረፍ እና ማውደም በአሸባሪው ቡድን እንደሁኔታው በቅደም ተከተል ተግባራዊ የተደረጉ የወረራ ስልቶች ነበሩ ነው ያሉት፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት በከተሞች እና ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመተኮስ፣ ሰርጎ ገቦችን እና የውስጥ ተላላኪዎችን መጠቀም እና ኹከት መፍጠር የአሸባሪው ቡድን ተቀዳሚ ተግባራት ነበሩ ብለዋል፡፡ የሽብር ተልእኮው እንደተጠናቀቀ በቀጣይ የሚገባው ቡድን ተግባሩ ማግባባት ወይም ማጭበርበር ነበር ተብሏል፡፡
አሸባሪው ቡድን “እኛ የምንፈልገው መንግሥትን ነው፤ እናንተን የማስተዳደር ሕጋዊ መብት የለንም፤ የጎበዝ አለቃ ምረጡ፤ የጦር መሳሪያ ያለው ብቻ ያስረክብ እና የሸሹ ንጹሐን ካሉ መልሷቸው” በማለት በነዋሪው ሕዝብ ዘንድ እምነት ለማግኘት ይሞክራሉ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ይህም የወረራው ሁለተኛ ክፍል ነበር ነው ያሉት፡፡ የዚህ ተልዕኮ አባላት የሕዝቡን መረጋጋት እና መዘናጋት ካዩ በኋላም ቦታውን ለሌላ አካል አስረክበው ይለቃሉ፡፡
በሦስተኛ የሚመጣው ቡድን በርካታ ቁጥር ያለው ከመሆኑም ባሻገር የተጠና እና የተደራጀ ተልዕኮ የያዘ ነው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ነው ይላሉ፡፡ የሕክምና፣ የምህንድስና፣ የመካኒኮች እና የተለያዩ ዘርፎች ቡድን ቀድሞ በተጠና መልኩ ወደ ከተሞች ከገባ በኋላ በየዘርፉ ተቋማትን፣ ፋብሪካዎችን እና የንግድ ድርጅቶችን ይቆጣጠራል ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላቸው ዘረፋውን ሙያዊ በሆነ መንገድ ይከውናሉ ነው ያሉት፡፡ በዘረፋ ቡድኑ የየዘርፉ ሙያ ካላቸው ግለሰቦች ውጭ ሊነቀሉ የማይችሉ የሕክምና፣ የምህንድስና እና የፋብሪካ ማሽኖች በጥንቃቄ ተነቅለው መዘረፋቸው በጥናቱ መረጋገጡን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም በየግለሰቦች ቤት ፍተሻ እና ብርበራ በማካሄድ የግለሰቦች ሃብትና ንብረት፣ ጌጣጌጥ እና ሙዳየ ምጽዋት ሳይቀር ተሰርቀዋል ተብሏል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንዳብራሩት በመጨረሻም አውዳሚ ወይም የአካባቢው ማኅበረሰብ “ጀሌ” በሚል የሚጠራቸው ገጀራ እና መሰል ስለታም ነገሮችን የያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቡድን ገብቶ ከዘረፋ የተረፉትን እና መንቀሳቀስ የማይችሉትን ሁሉ አውድሟል፡፡ የትምህርት እና የጤና ተቋማት የዚህ ቡድን ሰለባ ሆነዋል ነው የተባለው፡፡ የሕክምና እና የትምህርት መረጃዎች ተቃጥለዋል፤ ኮምፒውተሮች እና ሸልፎች ተሰባብረዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን የተወሰኑ አካባቢዎች ለዘጠኝ ቀናት በዘለቀው የአሸባሪው ቡድን ወረራ መጠነ ሰፊ ዘረፋ ተፈጽሟል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ በሌሎች አካባቢዎች ሊኖር የሚችለውን ጉዳት መገመት አዳጋች አይደለም ብለዋል፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው “አሸባሪው ቡድን በወረራው የተደራጀ፣ በባለሙያዎቹ የተደገፈ እና ከፍተኛ ሃብት ዘረፋ አካሂዷል” ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፡፡
ዘረፋውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳየት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ መንግሥት ጦርነቱን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ለማኅበረሰቡ እፎይታን መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ጉዳቶችን እግር በእግር ተከታትሎ በማጥናት ግልጽ ማድረግ፣ ለተጎጅዎች ድጋፍ ማድረግ እና የደረሰውን የሥነ ልቦና ጉዳት በተጠና መንገድ መጠገን ተገቢ እንደሆነም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ