
ባሕር ዳር፡ መስከረም 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉ ወጣቶች አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገረው ወጣት ጌታቸው ወርቁ እሱና ሦስት ወንድሞቹ የህልውና ዘመቻ ጥሪውን በመቀበል በግንባር ላይ መሆናቸውን ጠቅሷል።
አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን በመፋለም ጀብድ እንድፈፅም አደራ ተሰጥቶኛል ነው ያለው ወጣቱ።
በተለይ በዚህ ወቅት መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ልክ እንደወንድሞቹ ሁሉ እሱም ሀገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል።
እንደ ወጣት ወርቁ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉት ወንድማማቾቹ ወጣት ሄኖክ ጌታ እና ወጣት ሳሙኤል ጌታ ከቤት እናታቸው መርቀው እንደሸኟቸው ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ ሀገራችን ከውስጥ ባንዳና ከውጭ ጠላት ለመጠበቅ ኀላፊነት ተጥሎብናል ብለዋል።
ከደላንታ ወረዳ የመጡት ወንድማማቾቹ የሀገር ሰንደቅ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በሚሰማሩበት ግዳጅ ሁሉ እስከ ሕይወት መሰዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ ሙሀመድ ወጣቶቹ በሚሰጣቸው ግዳጅ ሁሉ ኀላፊነታቸዉን በሚገባ በመወጣት የሀገርን ሉዓላዊነት እንዲያስጠብቁ አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዋር አባቢ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ