
ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ እያለ የሚጠራው አሸባሪው ትህነግ የወቅቱ የኢትዮጵያ እዳ ሆኖ ዳግም ክህደት ፈፅሟል። ቡድኑ አሸባሪ፣ ከሀዲ፣ ወራሪ፣ ዘራፊ፣ አውዳሚ፣ ጨፍጫፊ፣ ደፋሪ መሆኑን ሁሉም አውቆታል።
አሸባሪው ትህነግ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን የፈፀማቸው ተግባራት የአደባባይ ሀቅ ሆኗል፤ የቡድኑንም ማንነት ይፋ ያወጣ ነው፡፡ ይህንን አሸባሪ ቡድን ነቅሎ ለመጣል መፍትሔው በፅናት መታገልና ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ንጹሐን እየተጨፈጨፉ፣ እየተራቡ እና መከራ እያዩ ባለበት በዚህ ወቅት ተዋግቶ ከማሸነፍ ውጭ ሌላ ምን መፍትሔ አለ? ምንም!
አሸባሪው ትህነግ ከቅድመ ወረራ በፊት…
ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ “ለውጊያ ዝግጁ ነን” የሚል መልእክት ያላቸው ወታደራዊ ሠልፎች፤ ተደጋጋሚ በእብሪት የተሞሉ የፓርቲ መግለጫዎች፣ መስከረምን አልፈውም ጥቅምት መግቢያ ላይ “ማእከላዊ መንግሥቱ ከመስከረም 30 በኋላ ቅቡልነት የሌለው ነው፤ ሀገሪቱም መንግሥት አልባ ናት” የሚለው አጀንዳ የተራገበበት መንገድ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ነበር።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም
ሽብርተኛው ትህነግ ማእከላዊ መንግሥቱን በበላይነት ድል ያደርግልኛል ብሎ የመጨረሻውን ቀይ መስመር ያለፈበት አልፎም ሁሉ ነገሩ ያከተመበት ዕለት ነው።
እንዲያውም የትህነግ ጉዳይ ከሚዲያ ፕሮፖጋንዳነት ባለፈ ሀገር ወደ መውረር፣ አይነኬው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የመፈጸም የክህደት ደረጃ ይደርሳል ብሎ የጠበቀም አልነበረም። ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሽብርተኛው ትህነግን የከሀዲነት እና ቀቢፀ ተስፋ ዓላማ የተረዱበት መጥፎ ክስተት ሆኖ አልፏል።
ማይካድራ …
ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ሽብርተኛው ትህነግ በማይካድራ አማራን የጨፈጨፈበት ምክንያት በማንነት ብቻ ለይቶ መሆኑን ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች አረጋግጠዋል። በጎንደር ዩኒቨርስቲ በተረጋገጠ ጥናት ከ1 ሺህ 500 በላይ የጅምላ ጭፍጨፋው ሰለባዎች ንጹሐንም በዋናነት የተገደሉት ሳምሪ በተባለ የሽብርተኛው ትህነግ ገዳይ ቡድን ነበር። የዚህ ቡድን አባላት አብዛኞቹ ወደ ሱዳን መሸሻቸው ይታወቃል።
ሕግ ማስከበር…
የሀገርን የሕግ የበላይነት ለማስከበር ለስምንት ወራት የሕግ ማስከበር ርምጃ ተከናውኗል። ቁልፍ የሽብርተኛው ትህነግ ሰዎች ያሠቡትን ሳያሳኩ ቀርተዋል። በርካቶች ተደምስሰዋል። በርካቶች ተማርከው ታስረዋል። ጥቂቶች ወደ ጫካ ሸሽተው ከርመዋል።
ዳግም ክህደት…
አሁን ሽብርተኛው ትህነግ ዳግም ወረራ የፈፀመበት ወቅት ነው። ችግሩም ከሕዝብ ጋር መሆኑን እያስመሠከረ ይገኛል። ወሯቸው ነፃ በወጡ አካባቢዎች ንጹሐንን በጅምላ እስከ መጨፍጨፍ የዘለቀ ወንጀል መፈፀሙ በሰሜን ወሎ በቆቦና አጋምሳ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎንደር በጭና እና ቦዛ በርካቶችን በጅምላ ጨፍጭፏል። በአፋር በጋሊኮማ በርካታ ንጹሐንንም ገድሏል፡፡ ዳሩ ካልተጠበቀ መሀሉ ዳር የማይሆንበት እድል የሌለ መሆኑን በርካቶች እየተረዱት ቢሆንም የጠላትን አካሔድ የሚመጥን አፀፋ እና ባጠረ ጊዜ ከምድረ ገፅ የማስወገዱ ጉዳይ ምርጫ የሌለው ምርጫ ነው። ሙሉ ኢትዮጵያን የመውረር አቅም ቢኖረው ምን አይነት ውጤት እንደሚኖር እስካሁን ወረራ ከፈፀመባቸውና ጥቃት ካደረሰባቸው አማራ እና አፋር ክልሎች መረዳት በቂ ነው።
አሁንም የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አረመኔያዊ ድርጊቱን ቀጥሎበታል፡፡ ይህንን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ሁሉም መታገል ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው፤ ለዚህም ሁሉም በአንድነት ይክተት፣ ይመክት፣ ያንክት!
በሀብተጊዮርጊስ አበይ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ