የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን መፈረካከስ በዓይን እማኝ አንደበት፡፡

380
መስከረም 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በማይጠብሪ ግንባር የገባው የትህነግ ወራሪ ቡድን መፈረካከሱን የዓይን እማኝ ለአሚኮ ተናግረዋል። በማይጠብሪ ግንባር ለወረራና ለዘረፋ የገባው አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድን አብዛኛው መደምሰሱን መዘገባችን ይታወሳል። በቡድኑ ላይ የደረሰበት ከባድ ምትም እንዲሽመደመድ አድርጎታል። የአሸባሪው ቡድን እንቅስቃሴ የሚቃኙት የዓይን እማኝ ለአሚኮ እንደገለጹት በመሪውና በተመሪው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አይሎ እርስ በእርሱ አፈሙዝ እስከ መዟዟር ደርሷል። ደባርቅ እና ዳባትን ተቆጣጥረናል ጎንደር ተዳርሰናል እያሉ በማስወራት የሰበሰቡት ወራሪ ቡድን እውነታውን ሲያውቅ ከመሪዎቹ ላይ ጠመንጃ ማዞሩን ነው የተናገሩት።
አሸባሪውና ወራሪው ቡድን በጭና ድባቅ ሲመታና ከወገን ጦር የሚደርስበትን ዱላ መቋቋም ሲሳነው በቡድን በቡድን እየሆነ መክዳቱን ነው የዓይን እማኞች ያረጋገጡት። እንደ እማኞች ገለፃ ከመሪዎቻቸው ጋር የማያገናኝ እና ተከዜን አሻግሮ ወደ ትግራይ የሚያስገባ መንገድ በመጠየቅ ሸሽተዋል። በጭና ላይ ሬሳ በሬሳ ሲሆኑ ከወገን ጦር ዱላ የተረፈው ወራሪ ቡድን ወደ መጣበት መመለሱን ነው የአይን እማኞች የተናገሩት።
በዛሪማ ሲደርሱም ‟እባካችሁን እህል ውኃ ከቀመስን ብዙ ቀን ሆኖናል፣ ያላችሁን ስጡን” እያሉ እንደለመኑና የበረቱት ደግሞ መቀማታቸውን ነው የገለጹት። አብዛኛው እግረኛ መሄድ እንዳቃተውና በየመንገዱ እንደሚወድቅም ገልጸዋል። ‟ጭና ላይ ስንደርስ መሪያችን ተመታብን፣ የሚያዋጋን የለም ተበተንን። ከዚህ በኋላ ውጊያ የሚባል አያሳየን፤ ወንድሞቻችን አልቀዋል” ብለውናልም ነው ያሉት።
እንደ እማኞች ገለፃ ከመራብና ከመድከማቸው የተነሳ ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸዋል። ዛሪማ ሲደርሱ ከኋላ የመጣ አንድ አዋጊ ብስኩት ብሉ ብሎ ቢሰጣቸው ‟እኛ ከእናንተ ምንም አንፈልግም አሁን ወደ ሀገራችን መመለስ እንፈልጋለን፣ ከእናንተ ጋር ሀገራችን ከደረስን በኋላ እንነጋገራለን፣ መንገድ ልቀቅ ካለቀቅክ እንገድልሃለን“ ብለው መሳሪያ ማዞራቸውንም ያነጋገርናቸው የአይን እማኙ ተመልክቸአለሁ ብለዋል።
አዛዡም ተደናግጦ መኪናውን አዙሮ ወደ መጣበት አቅጣጫ መሄዱን ነው የገለጹት። መሪዎቹ ‟በጫንቅ አድርገን ወጥተን ደባርቅ ነው ያለነው፣ ተከተሉን እያሉ ወስደው ነው ያስጨረሱን፤ በውሸት ድል ስንቅ ሳንይዝ እሳት ውስጥ አስገብተው አስጨረሱን” ማለታቸውንም ገልጸዋል። በታች የአጅሬ ጃኖራ፣ በላይ የጭና እና ሌሎች የስሜን ጎንደር አካባቢዎች የጥይት ቆሎ አቀረቡልን እንጂ አላስጠጉንም ብለውናልም ነው ያሉት። በጭና እና በአካባቢው ድባቅ ሲመታ ከኋላ ኀይል ሲጨምር የነበረው በርካታ መኪና መዋቅራቸው እንደፈረሰና አብዛኛው ተዋጊ በገባበት እንደቀረ ሲያውቅ መመለሱን ገልጸዋል። መኪና አንጠቀምም ብለው በርካቶቹ መሪዎቻቸውን ትተው ወደ መጡበት ቀዬ መመለሳቸውንም ተናግረዋል።
አሸባሪው ትህነግ በማይጠብሪ ግንባር የሰብዓዊ፣ የሥነልቦናዊና የቁሳዊ ክስረት እንደደረሰበትም አስረድተዋል። የወገንን ጦር መቋቋም የሚችል ኀይል እንደሌላቸውና አብዛኛው ወራሪ የመሪዎቹ ውሸት በተግባር ስለተገለጠለት የመዋጋት ሥነ ልቦና እንደሌለውም ተናግረዋል። አሸባሪው ቡድን የተከታዮቹን ሥነ ልቦና ለመጠበቅ የሚሞቱበትን ተዋጊዎች ገሚሶችን ገደል፣ ገሚሶችን ደግሞ ከሞላ ወንዝ ውስጥ እየጨመረ ለመደበቅ ጥረት አድርጓል።
ነገር ግን ብዙዎቹ ተያዙ ከተባሉት አካባቢዎች ሳይደርሱ ሲመለሱና ወደ ኋላ ሲሸሹ አብዛኞቹ ሳይመለሱ በመቅረታቸው የመሪዎቹ ስብከት ውሸት እንደነበር ማረጋገጥ ችለዋል። በዚህ የተነሳም አብዛኛው ወራሪ ቡድን ባልተጨበጠ እውነት እያለቀ በመቅረቱ ለመዋጋት ሞራሉ እንደሌላቸውም የዓይን እማኙ ነግረውናል።
በማይጠብሪ የተሰለፈው የጠላት ስብስብ መሪዎቹ በሰጡት ውሸት እና በተግባር ባዩት እውነት ልዩነት ተፈረካክሷል። በጭና አካባቢ የደረሰበት ምትም ቡድኑ እንዲዛባና ዳግም አገግሞ ለውጊያ ዝግጁ እንዳይሆን እንዳደረገውም ገልጸዋል።
በዛሪማ ከተማ ሲደርሱ አልቀናል፣ የተባልነው እና ያገኘነው ፈጽሞ አይገናኝም ማለታቸውንም ነግረውናል። ለዘረፋና ለውንብድና የተሰለፉት ወራሪዎች ዛሪማ ሲደርሱ ጎንደር ተዳርሰናል እያሉ ይጨፍሩ እንደነበርም አብራርተዋል። ደባርቅ የእኛ፣ ዳባትም የእኛ፣ ጎንደርም የእኛ እያሉ ሲጨፍሩ ተጭበርብረው እንደመጡ አስቀድመን እናውቅ ነበር ያሉን እማኞቻችን እንዳልነበር ሆነው ተመትተው ሲመለሱ አፍረው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና ከጋቦን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።
Next articleምርጫ የሌለው ምርጫ ! ማሸነፍ ብቻ!