
መስከረም 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ❝እናንት የትግራይ ልጆች ሆይ ድል ያለው ከእኛ ጋር ነው፣ የሚያሸነፍን የለም፣ የሚገፋን አይገኝም፣ መዳረሻችን አራት ኪሎ፣ ስልጣኑም የእኛ ነው፣ ደባርቅን ይዘናታል፣ ደባትን ተቆጣጥረናታል፣ ጎንደር እየደረስን ነው❞ እያለ የሕልም እንጀራ እያበላ ሕዝብ ይሰበስባል። የትግራይ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ የሕልሙን እንጀራ ሊመገቡ፣ በአማራ እንጀራ ሊጠግቡ ወደ ጦርነት ይመጣሉ።
ተከዜን እየተሻገሩ በውሸት ተይዛለች ከተባለችው ደባርቅ ሊያድሩ፣ በዛውም ሊሰነብቱ ጎረፉ። ሁሉ ቀላል፣ ሁሉም አልጋ በአልጋ ሆኖ የተነገራቸው ወራሪዎች ነገሩ የተገላቢጦሽ ነበርና በየመንገዱ የጥይት እራት እየሆኑ ቀሩ። እናቱን የሚሰናበት እንጂ ዳግም ሄዶ እናቴ መጣሁልሽ እንደምን ከረምሽ የሚል አልተገኘም። ሁሉም ባሩድ እየበላው፣ ረሃብ እየለጋው በዱር በገደል ይቀራል እንጂ። አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወራሪዎችን እየሰበሰበ እያመጣ ሲያልቅበት እየጨመረ ያስፈጅ ጀመር። በተለይም በጭና፣ በቦዛና በብና አካባቢ ሲደርስ እንዳልነበር ሆኖ ተመታ። አብዛኛው በገባበት ቀረ። የተረፈው ወደኋላ መፈርጠጥ ጀመረ። ወደኋላ የሚፈረጥጠውን ደግሞ በድብ ባሕር አድርጎ በዛሪማ የገባው የወገን ጦርና የአካባቢው ማኅበረሰብ ለቃቀመው።
ከመነሻ ቦታው እንዲዘርፍ ደባርቅ እና ደባት እንደተያዙ የተነገረው ወራሪ ሁሉ ውሸት እንደሆነ ሲረዳ ❝ወገኔ በእኛ የደረሰ በእናንተ አይድረስባችሁ❞እያለ እያለቀሰ ተመለሰ።
❝የዚያን የውሸት ቋት የትህነግን ነገር
ሰው ዝም ይበልና ዛሪማ ይመስክር❞ ስለ አሸባሪው ትህነግ ግፍ ዛሪማ እንደ ሰው ቢናገር፣ ያዬውን ቢመሰክር ዓለም በተደነቀ ነበር። የትህነግ ደጋፊዎችም አንገታቸውን በደፉ፣ የእናታቸውን ማሕጸን በተመኙ ነበር። ዳሩ ዛሪማ ይታዘባል እንጂ አይናገርም። ከዛሪማ ወንዝ ዳር፣ ከታላቁ የዛሪማ ድልድይ ግርጌ ነኝ። አሸባሪው ትህነግ ታላቁን ድልድይ ለማፍረስ ብዙ ጥሮ የአካባቢው ጀግኖች ሲያጣድፉት ጥሎ ፈርጥጧል። የተለያየ ቦታ ላይ ድልድዩን ቦርቡሮ ፈንጅ ማጥመድ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ከድልድዩ ግርጌ ከዛሪማ ነዋሪ ወጣቶች ጋር ተገናኝቻለሁ።
ሙክታር ኑሩሴን ይባላል። የዛሪማ ነዋሪ ነው። አሸባሪው ትህነግ በዛሪማ የፈፀመውን በደል ተመልክቷል። ከወንዙ ዳር ቁጭ ብለን በዛሪማ የሆነውን ሁሉ ያጫውተኝ ጀመር። ❝ውጊያ ሲካሄድ በወንዙ ዳርቻ ነበርኩ። ብዙ አስከሬን ነበር። ፈረስ የሌለውን ጋሪ ሁለት ሆነው ጋሪውን እየጎተቱ ስድስት ስድስት እያደረጉ ሰባት ጊዜ ዛሪማ ወንዝ እያመጡ ደፉ። ጋሪውን ድልድዩ ላይ ያቆሙና፣ የሞቱትን ሹራባቸውን ጫማቸውን እያወለቁ፣ ከድልድዩ ላይ ሆነው ወደ ሞላው ውኃ ይወረውሯቸዋል። ራቁታቸውን ነው የሚጥሏቸው። ያየሁት ነገር ከአዕምሮየ በላይ ሲሆንብኝ ወጥቼ ወደተራራው ሄድኩ❞
❝ትህነግ ጀሌዎቹን በጣም ቢወዳቸው
በጥይት ሲሞቱ አፈር እንዳይነኩ ወንዝ ላይ ጣላቸው❞ በጣም ስለሚወዷቸው አፈር እንዳይበላቸው፣ ምስጥ እንዳይነካቸው በውኃ ሙላት አስወሰዷቸው። ለእነርሱ ዓላማ ማስፈፀሚያ የመጡና የተሰውትን አፈር ነፍገዋቸዋል። ለአስከሬኑ ክብር አልሰጡም። እያዘኑ አልቀበሩም። ይልቅ ከረጅሙ ድልድይ አናት ሆነው ወደ ወንዙ በራቁታቸው ይጥሏቸው ነበር እንጂ። ይህ ለሙክታር ከባዱ ጊዜ ነበር። ሰው መሆን እስኪያስጠላው ድረስ በግፋቸው ተሳቀቀ።
❝ወንዝ ላይ የማይጥሉትን ኑ ቅበሩ እያሉ ያስቀብሩናል። እኔ ብቻዬን ሰባት ሬሳ ቀብሬያለሁ። እኔንም ሊገድሉኝ ጥይት እየተተኮሰብኝ ሮጬ ነው ያመለጥኳቸው❞ ነው ያለኝ። ታላላቅ ሰዎችን፣ መነኮሳትን እና ቀሳውስትን ሳይቀር ሲጋራ ካልሰጣችሁን እያሉ ስቃያቸውን ያበሏቸው እንደነበርም ነግሮኛል።
❝አስክሬኑ ወንዝ ላይ የሚጥሉት ዋናው ዓላማቸው ድል እያደረግን ነው እያሉ የሚያስከትሉት ሁሉ እንዳያይባቸው ነው። አስከሬን አያሳዩትም። ውኃው በጣም ሞልቶ ነበር። እያመጡ ይወረውሩታል ይዞት እልም ይላል❞ አለኝ ሙክታር ከድልድዩ አናት ቆመው ሲጥሉበት የነበረውን ቦታ በእጁ እያሳየኝ።
ድል እንጂ ሽንፈት የለም እየተባለ የመጣው ሁሉ ቀድሞት የመጣው ውኃ እየበላው መሄዱን አያውቁም። በዛሪማ ከተማ የራሳችሁን ሀብት መኪና ላይ ጫኑ እያሉ እያስጫኑ ሲዘርፉ መመልከቱንም ሙክታር ነግሮኛል።
❝አንድ ሕጻን ተዋጊያቸውን እግሩን ቆስሎ አመጡት። ቁስሉ ትንሽ ነበረች፣ መዳን ይችል ነበር። አይ አንተ ጊዜህን አታቃጥል ብሎ ጨረሰው። ከዚያ በፌስታል ጠቅሎ ኦራል ላይ ሰቀለው። የሚሞቱባቸውን እና ቆስለው የሚገሏቸውን በመኪና እየጫኑ ወደ ወንዝ ዳር ይዘዋቸው ይሄዳሉ። መሪያቸው ተመትቶ አንዳትነኩኝ አላቸው። መኪና ውስጥ ከገባ በኋላ ግን መታው። ከኋላ ያለው በሽብር እንዳይመለስ ቁስለኛም ሬሳም አይሄድም ገድሎ ወንዝ ላይ መጣል ነው❞ ብሏል።
በዛሪማ ድልድይ ሥር ከሙክታር ጋር ያገኘሁት አትርሳው ፈቃዴ ይባላል። ለእናቱም ለአባቱም ብቸኛ ልጅ ነው። እናቱን ያማቸው ስለ ነበር እሳቸውን ጥሎ የትም መሄድ አልቻለም። የትህነግ ወራሪ ቡድን ከተማዋ ሲገባም ከእናቴ ጋር ይግደሉኝ ብሎ ነበር የተቀመጠው። በዚያ መቆየቱም ብዙ ግፎች ሲፈፀሙ እንዲያይ አድርጎታል።
❝ሕዝቡን ተገን አድርገው ይዋጉ ነበር፤ መከላከያ ሠራዊት ንጹሐን ወደ አሉበት አይተኩስም። እነርሱም በከተማዋ ሆነው መከላከያው ንጹሐን ወደ አሉበት ከባድ መሳሪያ እንደማይተኩስ ስለሚያውቁ። እነርሱ በእኛ ውስጥ ተቀርቅረው ይታኮሳሉ። በከተማ ሲያልፉ በአስፓልቱ እንኳን አይሄዱም። በአስፓልቱ ሲያልፉ የአየር ጥቃት ይደርስብናል ብለው ሲለሚፈሩ በቤት ተጠግተው ነው የሚያልፉት❞ ብሎኛል።
በጭና ተመትተው ሲፈራርሱ ሌት ከቀን በእግር መመለሳቸውንም ነግረውኛል። የመጨረሻ የተመለሱት ከኋላችን ጥለውን እንደተመለሱ አናውቅም ነበር፣ እኛ አልቀናል፣ ረሃብም ጥይትም ገድሎናል ብለውናል ነው ያለኝ። ለውጊያ የሚመጡት ሕጻናት እንደሚበዙም ነግረውናል።
❝እኔ ባየሁት ሁሉ ራሴን ጠላሁ፣ የቆሰለባቸውን ተዋጊ ያመጡና ይጨርሱታል። ከዛ አንስተው ወደ ወንዝ ይወረውሩታል❞ ነው ያለኝ። ሰብዓዊነት የሚባል ነገር አያውቁምና።
የዛሪማ ወንዝ ብዙ አስከሬን እየያዘ ይመጣ እንደነበርም ነግረውኛል። ብዙዎቹን ደግሞ ተኩስ ሲከፈት በድንጋጤ ወደ ወንዙ እየገቡ ዛሪማ ይዟቸው ሲሄድ ተመልክተዋል። ወደ ዬት እንደሚሄዱ ሳያውቁ የመጡ ተዋጊዎቻቸው ጦርነት ሲከፈት ያለቅሱ እንደነበርና ቤት እያስገቡ እንዲደብቋቸው ይመፀኗቸው እንደነበርም ነግረውኛል። ከኋላ የሚመጣው ወራሪ ቡድን ጎንደር ከገባው ጋር ለመገናኘት እየሄዱ እንደሆነ ይነግሯቸው እንደነበርም እነሙክታር ያስታውሳሉ።
በባዶ እግራቸው እየመጡ ያደረግነውን ጫማ እየቀሙ ይጫሙም ነበር። ❝የምንሄደው ለመሞት ነው፤ እንደማንመለስ እናውቀዋለን❞ ይሉን ነበርን ብለውኛል። እንዳሉትም አብዛኛው በገባበት ቀረ። ንጹሐንን እየሰበሰቡ የመከላከያን የሚመስል ልብስ እያለበሱ ምርኮኛ እያሉ እንደሚያስቀርፁም እነ ሙክታር ታዝበዋል። ምርኮኛ አመጣን እያሉ ተጨማሪ ሟች ይሰበስቡበታልና።
ሙክታር እና አትርሳው በዛሪማ ወንዝ ዳር በድልድዩ ግርጌ ተቀምጠው አያሌ ግፎችን ነገሩኝ። የነገሩኝ መዝግቤ፣ አመስግኛቸው ወደላይ ወጣን።
አሸባሪው ትህነግ ራሱ የበላቸውንና ያስበላቸውን ሁሉ እየሰበሰበ ወደ ወንዝ ይጥላል። የኢትዮጵያ እውነት የማይታያቸው ሁሉ እየተከተሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት የትግራይን ንጹሐን እየገደለ ወንዝ ላይ እየጣላቸው ነው ይላሉ። የአሸባሪው ትህነግም ውሸቱን የሚያገንነት ሁሉ ወዳጁ ነውና የደስታ ከበሮ እየመታ ወገኖቼን እየገደሉ ወንዝ ውስጥ ጣሏቸው ይላል። ዓለም እውነታውን መረዳት ከፈለገች በተከዜ፣ በዛሪማ እና በሌሎች ወንዞች ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎችን እየጠየቀች ትረዳ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ