
ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን 76ተኛ የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ኒዮርክ አሜሪካ የገቡ ሲሆን፤ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌይ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል መንግሥት በኀላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት መሬት ላይ ያለው እውነት ሊሸፈን እንደማይገባም አሳስበዋል።
ሰብዓዊ ስጋቶችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የሚገጥሙ ችግሮችን አብራርተዋል።
በሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ጋር መንግሥት በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይም ውጤታማ በሆነ አግባብ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥን በማመቻቸት ረገድ በመንግሥት ላይ ሚዛናቸውን ያልጠበቁ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ክሶች ተደጋግመው እንደሚነሱ በማስታዎስ፤ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በችግሩ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች በሙሉ ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቬንዙዌላ የውጭ ግንኙነት ሚኒስትር ፌሊክስ ራሞን ፕላስሴሲያ ጎንዛሌዝ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ኒውዮርክ ላይ መክረዋል።
በቀጣይ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና የትብብር ማዕቀፍ ለማስፋት ትርጉም አዘል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል አቶ ደመቀ ።
መረጃው የተገኘው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m