የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ብሔራዊ የደኅንነት ስጋቶችን በማስቀረት በኩል ስኬታማ ሥራዎች ማከናወኑን አስታወቀ።

242

አዲስ አበባ: መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ2013 ዓ.ም በሀገር አንድነትና ህልውና ላይ የተደቀኑ ብሔራዊ የደኅንነት ስጋቶችን አስቀድሞ በማምከን በኩል ስኬታማ ሥራዎች ማከናወኑን  ገልጿል። 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ2013 የሥራ ዘመን የማጠቃለያ የዕቅድ አፈጻጻም ላይ ጥልቅ ግምገማ በማድረግና በ2014 የሥራ ዘመን ዕቅድ ዝርዝር ተግባራት ዙሪያበመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።       

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመሥገን ጥሩነህ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፈው የበጀት ዓመት ሀገራዊ አንድነትን ለማፍረስ ዒላማ ያደረጉ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን በመቀልበስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። 

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በተለይ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ  ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን  በማድረግ በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫ ቀንና ከምርጫ በኋላ ሂደቱ ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፌደራልና ከክልል የደኅንነትና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ጉልህ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ የ2ኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ የተጣለበትን ተቋማዊ ኀላፊነት በመወጣት  ቁልፍ ሚና ማበርከቱን አቶ ተመሥገን ገልጸዋል።    

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ካለው የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ወሳኝ የመረጃ ስምሪቶችን በማከናወንና አመራር በመስጠት የተደቀነውን ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት በማስቀረት በኩልም ተልዕኮውን  ተወጥቷል ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራሉ።     

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱን የመፈጸም  አቅም  ለማሳደግ  ባለፈው ዓመት በተለይ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሎጀስቲክስ፣ ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር በኩል በርካታ ሥራዎች በትኩረት ሲሠሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተመሥገን፣ የውስጥና የውጭ ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድም ውጤታማ ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም የተቋሙን አፈጻጻም የሚያሻሽሉ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥራዎች  እንደሚከናወኑ አያይዘው ጠቁመዋል። 

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱም የሀገር ህልውናና አንድነትን ለማስጠበቅ ሕወሓትን ጨምሮ በሽብርተኞች ላይ መወሰድ ከተጀመረው የተቀናጀ እርምጃም ጋር በተያያዘ ተቋማዊ ተልእኮን የመወጣቱን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሱት አቶ ተመሥገን፤ በቀጣይ የሚከናወነው የ3ኛው ዙር የህዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ሌሎች ዓበይት የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን ለማስቀረት ከፌደራልና ከክልል የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱን እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል፡፡ 

በ2014 የበጀት ዓመት ዓለም አቀፋዊ፣አህጉራዊ፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ የደኅንነት ስጋቶችን በመተንተን የሀገር ብሔራዊ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ፤ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን ጠንካራ ፕሮፌሽናል ተቋም ለመገንባት የተጀመሩትን ፈርጀ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ ጠቁሟል። 

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

በዌብሳይት amharaweb.com

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየዘንድሮው የመስቀል በዓል ሲከበር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በማሰብ ሊሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገለጸች፡፡
Next articleበሰሜን የሀገሪቱ ክፍል መንግሥት በኀላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት እውነቱ ሊሸፈን እንደማይገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።