
ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
ደቡብ አፍሪካን አላፈርስም—ናሽናል ፓርቲ (አፓርታይድ)
ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ —ትህነግ (ብሔር-አፓርት)
ለ 46 ዓመታት ፓርቲያቸው ከያዘው ስልጣን ሲወርድ ጥቁር የሚገዛት ደቡብ አፍሪካ ትፍረስ አላሉም፤ በቀላሉ ማፍረስ እየቻሉ፡፡ እስረኛየ የነበረው ጥቁሩ ማንዴላ ከሚያስተዳድረኝ ጫካ እገባለሁ አላሉም፡፡ ምክንያቱም ስልጡኖች ነበሩ፡፡ ስልጡን ሰው ደግሞ ከለውጥ ጋር አብሮ ይለወጣል፡፡
የአፍሪካ ቀንድን ለጊዜው ባለበት ትተን ወደ ደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል እናምራ፡፡ በህንድ ውቅያኖስ የተቀነፈ ድንቅ መልክዓ-ምድር የታደለች ወርቅ፣ እንቁ እና አልማዝ በከርሷ አምቃ የያዘች የውበት እና የጸጋ ምድር ናት-ደቡብ አፍሪካ፡፡ ማራኪ መልክዓ-ምድሯ የከበረው አፈሯ ለቀየው እንግዳ የሆኑ መርከቦችን ጠራ፡፡ ከመርከቦቹ የወረዱ ነጫጭ ጉዶችም ቀየዋን ተዟዙረው ቃኙ፡፡ ካርታም አነሱ፡፡ መርከቦቹ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው ጨመረ፡፡ የቀየው ባለሀገሮችም ነጮቹ ይሄዳሉ ብለው በማሰብ አልተተናኮሏቸውም፡፡ እነዚያ ነጫጭ ጉዶች ግን ድንኳኑን ወደ ቪላ መቀየር ጀመሩ፡፡ አካለው በሰፊው ማጠር ሲጀምሩ ነበር ዙሉዎች ጦራቸውን ወደ ነጮቹ መወርወር የጀመሩት፡፡ አልሳቱም ታዲያ፡ ነጮቹ ወደቁ፡፡ “ለካ ይወድቃሉ እነዚህ ጉዶች” ብለው ተገርመው ሳይጨርሱ ዙሉዎች መውደቅ ጀመሩ፤ ረገፉ፡፡ ለካ ነጩ ጉድ አንግቶት የሚዞረው ነገር በርቀት የሚገድል ጠመንጃ ነበር፡፡
የደች ኢስት ኢንድያን ኩባንያ እኤአ በ1652 በኬፕታውን መመስረቱ በደቡብ አፍሪካ የጭቆና ዘመን መምጣቱን ያረዳ አጋጣሚ ነበር፡፡ በ1815ም ብሪታንያ ኬፕታውንን በቅኝ ግዛት ያዘች፡፡ የቅኝ ግዛት ግፍን የመታገል ዘመቻው የደች እና እንግሊዝ ሰፋሪዎች ደቡብ አፍሪካ መስፈር ከጀመሩ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ የቀጠለ ነበር፡፡
ኔልሰን ማንዴላ ወደ ስልጣን ከመጡ እኤአ ከ1994 በኋላ ግጭቱ እንደ ቀድሞው የከፋ ባይሆንም የጸረ ጭቆና ትግሉ በተለየ ስልትና አካሄድ ቀጥሏል፡፡ ዛሬም ብዙሃኑ ደቡብ አፍሪካውያን የኢኮኖሚ ባርነት ውስጥ ነን የሚል ያደረ ቅሬታ አላቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ አሁንም ብርቱ ጥያቄዎች ከፊቷ ያሉባት ሃገር ብትሆንም በሁሉም መስክ ጠንካራ የምታባል የተከበረች ሃገር ነች፡፡ ነገም ተስፋዋ ትልቅ ነው፡፡ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት ትግል ረጅም ታሪክ ያለው ቢሆንም በተለይ በ1950ዎቹ በልዩ ሁኔታ ተጠናከረ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ናሽናል ፓርቲ በ1948 ባልተጠበቀ ሁኔታ ዩናይትድ ፓርቲን አሸንፎ ወደ ስልጣን የመምጣቱ አጋጣሚ ነበር፡፡
የደች ዝርያ ባላቸው ነጮች የሚመራው ናሽናል ፓርቲ መንግስት መሆኑን ተከትሎ አፓርታይድ የተባለ ፓሊሲውን አውጥቶ ተገበረ፡፡ አፓርታይድ መሰረቱ (Apart) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው፡፡ እንደወረደ ቃሉ ተነጣጥሎ መቆምን ወይም በሁለት ነገሮች መካከል ክፍት ቦታ መኖርን ያመለክታል፡፡
የአፓርታይድ ጠቅላላ መንፈስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መለያየት ነበር፡፡ የሚለያዩበት መሰረታዊ መስፈርት ደግሞ ዘር ወይም የቆዳ ቀለም ነው፡፡ በዚህ መሰረት ሰዎች በ 3 ተከፍለው ነበር፡፡ ነጭ (white)፤ድቅል (Coloured) እና ጥቁር (black)፡፡ እነዚህ ቀለሞች በሃብት እና በድህነት በነጻነት እና በባርነት መካከል ያሉ ልዩነት ፈጣሪ ነገሮች ነበሩ፡፡ ነጩ ከፈጣሪ ቀጥሎ የምድሯ ገዥ ነበር፡፡ ጥቁሩ እንደ መሬቱ ሁሉ የነጩ ንብረት ሆኖ ኑሯል፡፡ አፓርታይድ ክፋቱ በቆዳ ቀለም ተመስርቶ ለነጩ ጥቅም መቆሙ ብቻ አይደለም፡፡ የነጩን ሰብዓዊ መብት እንኳ የሚጥስ መሆኑ ነበር፡፡ ይህ የአፓርታይድ ከፋፋይ ህግ እንኳንስ እንዲጨቁናቸው የተፈረደባቸው ጥቁሮችን ቀርቶ የነጮችን ነጻነት የሚገድብ ነበር፡፡ የአፓርታይድ ፓሊሲ ያስከተለው ግፍ እየተባባሰ መጥቶ የህዝብን ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡
የብዙሃኑ ጥቁሮች ግፍን የመታገል እንቅስቃሴ እድሜ በአፍሪካ ለተቀጣጠለው የነጻነት ትግል አዲስ ቅርጽ ተላበሰ፡፡ የተበተነው ሕዝባዊ ትግል በፓርቲ መሪነት ተገምዶ ጠላቶቹን ጠልፎ የሚጥል ብርቱ ገመድ ሆነ፡፡ የሕዝቡ የነጻነት ትግል በጨመረ ቁጥር በጥቂት ነጮች ብቻ የሚሾረው የናሽናል ፓርቲ የበቀል በትሩን አበረታ፡፡ ለሰልፍ የወጡ ጥቁሮች አስከሬናቸው ጎዳናዎችን መሙላቱ የተለመደ ሆነ፡፡ የጥቂት ነጮች መንግስት የሕዝቡን ድምጽ ለማፈን ሁሉንም አማራጮች ተጠቀመ፡፡
ሰላማዊ የትግል ስልትን ብቻ ለመከተል የወሰነው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ (ANC) በሰላማዊ መንገድ ትግሉ ፍሬ የማፍራቱ ነገር አልታይህ አለው፡፡ፓርቲው የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ ወታደራዊ ክንፍ አቋቋመ፡፡ የፓርቲው መሪ ኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ክንፉን ለማጠናከር ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ አዲስ አበባ የተገኘውም በዚያ አጋጣሚ ነበር፡፡ ገዥው የወቅቱ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ እና መሪውን መንግስትን በኀይል በመለወጥ ወንጀል በሽብርተኝነት ከሰሰ፡፡
ማንዴላ ተይዞ ለ27 ዓመት ታሰረ፡፡ የማንዴላ እና ሌሎች የትግሉ መሪዎች መታሰር ግን የነጻነት ትግሉን ይበልጥ አጧጧፈው፡፡ ገዥው ናሽናል ፓርቲ ( አፓርታይድ) በበኩሉ አፈናውንና ግድያውን አጧጧፈ፡፡ ሁኔታው ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያመራ በቋፍ ላይ ሆነ፡፡ ጥቁሮች እንደ አፓርታይድ ዘመናዊ መሳሪያ ባይታጠቁም ለመሞት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ሀገር ምጥ ላይ ሆነች፡፡ ነገሮች በአንዳች ታምር መፍትሔ ካላገኙ ውቧ ባለጸጋ ምድር ለነጮችም ለጥቁሮችም የማትሆን አኬልዳማ (የደም መሬት) የመሆኗ አይቀሬነት በየእለቱ ከሁለቱም ወገን በሚነሱ በደም የተለወሱ አስክሬኖች ምልክቱ ከበቂ በላይ እየታየ ነበር፡፡
ለውጥ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል በመጨረሻም ይሞታል፡፡ በአብራኩ ክፋይ ምናልባት ይቀጥላል፡፡ ይህ የለውጥ ሕግ ለፕሬዘዳንትም ሆነ ለቀን ሰራተኛ ይሰራል፡፡ ምንም ሁን ምን በተፈጥሮ የለውጥ ህግ ትዳኛለህ፡፡ በማኅበራዊም ሆነ በፓለቲካው ለውጥ አይቀሬ ሕግ ነው፡፡ ተወልዶ የማያረጅ የማይሞት የፖለቲካ ርዕዮት የለም፡፡ የደቡብ አፍሪካው የወቅቱ ገዥ ፓርቲ ከዚህ የለውጥ ህግ ጋር ነበር የተላተመው፡፡
የአፓርታይድ የነጭ የበላይነት የፓለቲካ ርዕዮቶችን ህዝብ በቃኝ ብሎ ሊቀብራቸው ተነስቷል በ1990፡፡ ናሽናል ፓርቲ (አፓርታይድ) ሁለት ምርጫዎች ብቻ ነበሩት፡፡ ከማይቀረው ለውጥ ጋር ተላትሞ አጥፍቶ መጥፋት ወይም ለውጡን ተቀብሎ አብሮ ከአዲሱ ዘመን ጋር መዘመን፡፡ ምርጫው ቀላል አይደለም፡፡ ትናንት ጥቁር በመሆኑ ብቻ ከጎኔ መቀመጥ አትችልም ብለህ በትምህርት ቤትህ ድርሽ እንዳይል ያደረከው ፤ትናንት አብሮኝ አያመልክም ብለህ ከሃይማኖት ተቋም ያሳደድከው “ሀገሬ የኔ ናት ልመራት ይገባል” ሲል ይህን ማስተናገድ በተለይ ለነጭ የበላይነት አራማጆች ከጦርነትም የከፋ ከባድ አጋጣሚ ነበር፡፡

ደቡብ አፍሪካን ለ46 ዓመት እግር ከወርች አስሮ የገዛው ናሽናል ፓርቲ (አፓርታይድ) በዚያ የምጥ ወቅት በ1989 አዲስ መሪ ሾመ፡፡ ዲ ደብሊው ዲ ክለርክ የሚባሉ፡፡ እንግሊዛዊ ቅላጼ በተላበሰ ንግግራቸው የሚታወቁት ዲ ክለርክ አሰቡ፡፡ ተጨነቁ፡፡ የእርሳቸው ውሳኔ ወይ ሀገር ያድናል አልያም ያፈርሳል፡፡ በፓርቲያቸው አባላት የተሞላው ነጮች የሚፈነጩበት ምክር ቤት የካቲት 2/ 1990 ጉባኤ ነበረው፡፡ አፓርታይድ በጥቁሮች ላይ በሚፈጽመው የጅምላ ግድያ ደቡብ አፍሪካ የማዕቀብ ሰለባ ሁናለች፡፡ ሀገሪቱ ከውስጥም ከውጭም ተወጥራ ባለችበት ጊዜ የሚደረገውን የምክር ቤት ጉባኤ ለመዘገብ የብዙኀን መገናኛዎች በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ ነጩ ማንዴላ ዲ ክለርክ “አፓርታይድ ስህተት መሆኑን አምነን ከልብ የመነጨ ይቅርታ ጠይቀናል፡፡ በቃል ብቻ አይደለም በተግባርም አፓርታይድን የማፍረስ ስራ ሰርተናል” ዲ ክለርክ ዲ ክለርክ ወደ አትሮንሱ ቀርበው ይህን አሉ፡፡
“የተላለፉ ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ፣የፓን አፍሪካን ኮንግረንስ፣የደቡብ አፍሪካ ኮሚኒስት ፓርቲ ላይ የተጣለው እገዳ ተነስቷል፡፡…ኔልሰን ማንዴላ እና ሌሎች የፓለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ተወስኗል፡፡” ዲ ክለርክ ይህን ሲናገሩ አክራሪ ነጮች ወዲያውኑ ከአዳራሹ ወጥተዋል፡፡ ዲ ክለርክ በዚያ ቀን ያደረጉት ንግግር የሀገሪቱን ታሪክ የቀየረ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በዲ ክለርክ መሪነት ከ1989-94 ስር ነቀል ለውጥ አስተናገደች፡፡ ለውጡ የአፓርታይድ ፓሊሲን መቀየር ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቀለም ልዩነት ያልታየበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በ1994 አደረገች፡፡ በዚህ ምርጫ የጥቁሮቹ የነጻነት ታጋይ የነበረው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ አሸናፊ ቢሆንም አስገራሚው ክስተት አፓርታይድን ያስተዋወቀው ናሽናል ፓርቲ የርዕዮት ለውጥ አድርጎ በምርጫው መወዳደሩ ነበር፡፡ በዚሁ ምርጫ ናሽናል ፓርቲ 88 ወንበሮችን አሸነፈ፡፡ በማንዴላ ፕሬዚዳንትነት በተመሰረተው አዲስ መንግስት አምስት የካቢኔ ወንበሮችን አሸነፈ፡፡ የፓርቲው መሪ የነበሩት ዲ ክለርክ ከታቦ ምቤኪ ጋር የማንዴላ ምክትል ሆነው ተሹመዋል፡፡
በ1993 የኖቤል የሰላም ሽልማት ለማንዴላ ሲሰጥ ለውጡን በመምራት ፓርቲያቸውን እና ሀገራቸውን ወደ አዲሱ ዘመን ያሻገሩት ዲ ክለርክም ከማንዴላ ጋር ሽልማቱን ተጋርተዋል፡፡ ዲ ክለርክ የቀድሞ እስረኛቸውን አለቃቸው አድርገው የተቀበሉ ተራማጅ ጀግና ናቸው፡፡ በየካቲት 2020 ዲ ክለርክ ከ ቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን አሉ፡፡ “በደቡብ አፍሪካ ለመጣው ለውጥ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ጉልህ ሚና ነበረው፡፡ ግን ደግሞ ናሽናል ፓርቲም በተመሳሳይ ጉልህ ድርሻ ነበረው፡፡ አፓርታይድ ስህተት መሆኑን አምነን ከልብ የመነጨ ይቅርታ ጠይቀናል፡፡ በቃል ብቻ አይደለም በተግባርም አፓርታይድን የማፍረስ ስራ ሰርተናል፡፡ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ በትጥቅ ትግል እንደማያሸንፍ ራሱም ያውቀዋል፡፡ ሁለታችንም ነን ለውጡ እውን እንዲሆን ወሳኝ ሚና የተጫወትነው” ይህን ያሉት የመጨረሻው የአፓርታይድ መሪ የሚባሉት ዲ ክለርክ ናቸው፡፡
ለ 46 ዓመት ፓርቲያቸው ከያዘው ስልጣን ሲወርድ ጥቁር የሚገዛት ደቡብ አፍሪካ ትፍረስ አላሉም በቀላሉ ማፍረስ እየቻሉ፡፡ እስረኛየ የነበረው ጥቁሩ ማንዴላ ከሚያስተዳደረኝ ጫካ እገባለሁ አላሉም፡፡ ምክንያቱም ስልጡን ሰው ናቸው፡፡ ስልጡን ሰው ደግሞ ከለውጥ ጋር አብሮ ይለወጣል፡፡ በዚህ አውድ ዲ ክለርክ ከማንዴላ እኩል የለውጥ አርበኛ ናቸው፡፡ የአፓርታይድ መሪ የነበሩ ቢሆንም ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ሲረዱ ድርቅ ብለው አልቀሩም፡፡ ለውጡን አገዙ አፋጠኑት፡፡ ፓርቲያቸውን ሀገራቸውን ለውጠው ሁለቱንም ከጥፋት ታደጓቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከትላንቷ ጋር የታረቀች የተስፋ ምድር እንድትሆን ያደረጉ ጀግና ታጋይ ነጭ ማንዴላ ናቸው ዲ ክለርክ፡፡

ቁሞቀሩ ብሄር-አፓርት (ትህነግ) አፓርታይድ ዘረኛ ጨቋኝ ቢሆንም ስልጡን ነበር… እንደ አፓርታይድ ሁሉ ትህነግ ዘረኛ ርዕዮት ይከተላል፡፡ ሰዎች አንድ ላይ መቆማቸውን በስጋት ይመለከተዋል፡፡ ሰዎችን በቀላሉ መግዛት የምችለው ሲነጣጠሉ ነው ብሎ ያምናል እንደ አፓርታይድ፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ልዩነቱ ያለው ሰዎችን መነጣጠያ መስፈርቱ ላይ ብቻ ነው፡፡ ናሽናል ፓርቲ (አፓርታይድ) የቆዳ ቀለምን የመለያያ መስፈርት ሲያደርግ ትህነግ ብሄርን መሰረት ያደርጋል፡፡ በአጭሩ የትህነግን ርዕዮት (ብሄር- አፓርት) ልንለው እንችላለን፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች የጥቂቶችን አገዛዝ ብዙሃኑ ላይ ጭኖ ለመኖር የከፋፍለህ ግዛው መርህን ተግብረዋል፡፡ አፓርታይድ ማንዴላን ለ 27 ዓመት አስሮ አሰቃይቷል፡፡ ትህነግም ኢትዮጵያን ለ 27 ዓመት በግፍ አሰቃይቷል፡፡ በዘረኛ ፓሊሲዎቹ ከአፓርታይድ የማይተናነሰው ትህነግ ግን የናሽናል ፓርቲ (አፓርታይድን) የሚያክል የፓለቲካ ንቃት የለውም፡፡
አፓርታይድ ዘረኛ ጨቋኝ ቢሆንም ስልጡን ነበር፡፡ ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ሲረዳ ከለውጡ ጋር አብሮ ዘምኗል፡፡ ትህነግ ችካል ነው፡፡ ህሊናዊ መቀንጨር ያጠቃው ድርጅት በመሆኑ ከለውጥ ጋር ተላትሟል፡፡ የሕዝብ ትግል የፈጠረው የለውጥ ማዕበል አይቀሬ መሆኑን ተቀብሎ ራሱን ወደ አዲሱ ዘመን ማሻገር ተሳነው፡፡ በእብሪቱ በለኮሰው እሳት በትግራይ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መከሰት ያልነበረበት መከራ አስከትሏል፡፡ ቀይ መስመሩን አልፎ የሀገር ጠባቂ ሰራዊት ላይ ቃታ ከሳበ፤ይህም ምን ያክል ዋጋ እንደሚያስከፍል ከተመለከተ በኋላ እንኳ የአቋም ለውጥ ለማድረግ አልቃጣውም፡፡ ጭራሽ አገርሽቶበት አፓርታይድ ያልደፈረውን ደፈረ፡፡ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን፡፡” ይህ የትህነግ ቁሞ-ቀርነት እና እብደት አፓርታይድን እንድታደንቅ ያደርግሃል፡፡ ምክንያቱም አፓርታይድ እንደ ትህነግ በዘረኛ ርዕዮቱ ሚሊየኖች ላይ መከራ ቢያመጣም ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ሲረዳ ከለውጡ ጋር አብሮ ዘምኗል፡፡ እራሱም ተሻግሮ ሀገር አሻግሯል፡፡ ሀገር ማፍረስ እየቻለ አላደረገውም፡፡
የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቅ የፖለቲካ ሽግግር የሚባለው የደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ጀግኖቹ እነ ማንዴላ ብቻ አልነበሩም፡፡ የተከተሉት ርዕዮት የተሳሳተ እንደሆነ ተረድተው ይቅርታ ጠይቀው አፓርታይድን ያፈረሱ የአፓርታይድ መሪዎችም ጀግኖች ናቸው፡፡ ታዲያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያም ሆነ አፍሪካ የሚያስፈልጓት ለለውጥ የሚታገሉ ማንዴላዎች ብቻ አይደሉም፤ ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ተረድተው አብረው የሚለወጡ ዲ ክለርኮች ጭምር እንጅ፡፡
በዮሐንስ ልጅዓለም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ