❝አባት እና እናታችን ወታደር ሆነን የሀገራችንን ዳር ድንበር እንድናስከብር መርቀውና አበረታተው ነው የሸኙን❞ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተሸኙ ወንድማማቾች

238
ደብረ ታቦር: መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድንና ጀሌዎቹን ለመደምሰስ የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች በነቂስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለዋል።
ወጣቶቹ ዛሬ በደብረ ታቦር ከተማ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።
ሠራዊቱን ከሚቀላቀሉት መካከል የአንድ ቤተሰብ ወንድማማች ይገኙበታል።
ወንድማማቾቹ በጋራ ክንድ ጠላትን ድባቅ ለመምታት መነሳታቸውን ነው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የገለጹት።
ከላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተሸኘው ተመሥገን ተስፋዬ ከታናሽ ወንድሙ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ቆርጠው እንደተነሱ ነው የተናገረው።
❝አባቴ ወታደር ነበር፤ ስለውትድርና እና ስለ ሀገር ፍቅርም እያስተማረኝ ነው ያደኩት፤ ሆኖም ወደ ውትድርናው ዓለም ለመግባት አስቤም አላውቅም ነበር፤ ጠላት ከተማችን ገብቶ የሠራውን በደልና ግፍ በማየቴ ወታደር ሆኜ ጠላትን ለማጥፋት ቆርጬ ተነስቼያለሁ❞ ብሏል።
የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን ነፋስ መውጫ ከተማን በወረረበት ወቅት የዕለት እንጀራቸውን እንኳ ሳይቀር እንደነጠቀ እና በርካቶችን ለቀናት ጾም እንዲያድሩ ማድረጉን ተናግሯል።
❝አባቴና እናቴ ከታናሽ ወንድሜ ጋር በመሆን ወታደር ሆነን የሀገራችንን ዳር ድንበር እንድናስከብር መርቀውና አበረታተው ነው የሸኙን፤ እኔም ሆነ ታናሽ ወንድሜ ዓላማችንም ልባችንም አንድ ነው፤ ከመከላከያ ሠራዊት የትግል ጓዶች ጋር በመሆን ሀገራችንን ከባንዳና ከወራሪ መጠበቅ ነው❞ ብሏል።
አንዳንድ ወጣቶች ከደባል ሱሳቸው ተላቅቀው ወደ ትግሉ እንዲቀላቀሉም መልዕክቱን አስተላልፏል።
ሌላው ታድሏል ተስፋዬ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ከልጅነቱ ጀምሮ ውትድርናን ሲመኝ እንደነበረ ተናግሯል።
ከታላቅ ወንድሙ ጋር በመሆን መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀሉ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል፡፡ ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ ሀገሩን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ጊዜው የህልውና ዘመቻ ስለሆነ ወጣቱ ወደ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል ሀገሩን እና ሕዝቡን እንዲያድን ጠይቋል ።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከደብረ ታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጥናት በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ሊደረግ ነው።
Next articleየሁለት ዘረኞች ወግ