አሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጥናት በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ሊደረግ ነው።

371
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ በበርካታ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች የፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚመለከት ጥናት አካሂዷል፡፡
በጥናቱ መሰረትም የሽብር ቡድኑ ዋና የሚባሉ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸመ አመላክቷል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ገና ከምስረታው ጀምሮ የትግል ስልት እና ቴክኒክ አድርጎ ከተጠቀመው መንገድ መካከል አንዱ አማራ ጠል ትርክት ይጠቀሳል፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ገደማ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ከፈጸመው አስነዋሪ ክህደት በኋላም ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጥላቻ በተለየያየ አጋጣሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያካሂድ ከነበረው የስምንት ወራት የሕግ ማስከበር ቆይታ በኋላ በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ ሲደርስ አሸባሪው ትህነግ የሽብር ተግባሩን የፈጸመው በተለመደው የአማራ ጠል ትርክቱ “በአማራ ሕዝብ ላይ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ” በሚል ሽብር ነበር፡፡ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎችም ከንጹሐን ግድያ እስከ ተቋማት ዘረፋ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል ነው የተባለው፡፡
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች በወረራ የፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚመለከት ጥናት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡ ዐቃቤ ሕግ እና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በተለይም ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት ሽብርተኛው ትህነግ በወረራቸው አካባቢዎች የፈጸማቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው ብለዋል፡፡
የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ከፈጸማቸው ወንጀሎች መካከል በንጹሐን ላይ የተፈጸመ ግድያ አንዱ ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ከጦርነቱ ጋር ምንም አይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ንጹሐን በጅምላ እና በተናጠል ተገድለዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ የጀኔቫ፣ የሄግ እና የካምፓላ ስምምነትን በጣሰ መንገድ ትጥቅን መሰረት ባደረገ የሀገር ውስጥ ጦርነት ዜጎች ሕይዎታቸውን እንዲያጡ ማድረጉ ሌላው ወንጀል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ጥናቱ አካባቢዎቹ ከጦርነቱ ነፃ በወጡ ማግስት የተካሄደ በመሆኑ የተጎጅዎች ቁጥር ተፈናቃዮች ሲመለሱ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና የቀጣይ እጣ ፋንታቸው ያልታወቁ ዜጎች ቁጥርም በርካታ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው ብለዋል፡፡
የዜጎች የሀገር ውስጥ መፈናቀል በአሸባሪው ትህነግ የተፈጸመ ሌላኛው ዓለም አቀፋዊ ወንጀል መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ያመላከቱት፡፡
የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ብቻ ከ65 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በካምፓላ ኮንቬክሽን ትጥቅን መሰረት ያደረገ ግጭት ሲፈጠር ንጹሐን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዳይፈናቀሉ በታጣቂ ኀይሎች ላይ ግዴታ መቀመጡን አቶ ቴዎድሮስ አንስተዋል፡፡ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን ግን አስገድዶ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባቸው አካባቢዎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ከመተኮስ ጀምሮ በሰርጎ ገቦች እና በውስጥ ተላላኪዎች አማካኝነት በሕዝቡ መካከል ሽብር በመንዛት ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና የእምነት ተቋማትን መዝረፍ፣ የግለሰቦችን ሃብትና ንብረት መስረቅ እና ያልቻሉትንም የማውደም ወንጀሎችን ፈጽመዋል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛው አሸባሪው ቡድን በዞኑ የፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሴቶች ላይ የተፈጸመ አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ባርነት ነው ተብሏል፡፡ የአስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ባርነት ካላቸው ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጫና አንፃር የወንጀሉን መጠን ማወቅ ከባድ ነው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ አሸባሪው ትህነግ በዞኑ በወረራቸው አካባቢዎች የፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል አስከፊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላት ከ48 ዓመት አዛውንት እስከ 15 ዓመት ወጣቶች ላይ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ አንዳንዶቹ ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው በኋላ ተሰውረው የት እንዳሉ እንኳን አይታወቅም ነው ያሉት፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላት ከሃይማኖት ተቋማት ደርሰው ሲመለሱ የተገኙ ሴቶችን ጨምሮ በእያንዳንዱ ቤት ለዘረፋ ሲዘዋወሩ ባገኟቸው ሴቶች ላይም ወሲባዊ ባርነት እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽመዋል፡፡
ሌላው በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመው አራተኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት “ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” በሚል የሚገለጽ መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ አብራርተዋል፡፡ይህ የመብት ጥሰት የኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፣ ጥቃት እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ዒላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች በግፍ የገደሉትን ግለሰብ አስከሬን ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆን አንስቶ የተጎጂ ቤተሰቦች ለ11 ቀናት ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንዳያዝኑ፣ ሰው እንዳይደርሳቸው እና እንዳያለቅሱ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ ለሦስት ቀናት ሰውን ራቁቱን ዘቅዝቆ ማሰር፣ ግርፋት እና ክብረ ነክ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩ ዜጎች መሰረታዊ ትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲያገኙ ከሚደነግገው ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ ባሕላዊ እና መብቶች ቃልኪዳን በተፃራሪ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲወድሙ ተደርገዋል ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፡፡
አቶ ቴዎድሮስ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን በወረራቸው አካባቢዎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን እንደፈጸመ በጥናቱ መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡ የወንጀል ድርጊቶቹ በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቁ ናቸው ነው ያሉት፡፡
ጥናቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሰነድነት እንዲያገለግል ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየጎንደር ከተማ በጎፈቃደኛ ወጣቶች ለህልውና ዘመቻው የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እያካሄዱ ነው።
Next article❝አባት እና እናታችን ወታደር ሆነን የሀገራችንን ዳር ድንበር እንድናስከብር መርቀውና አበረታተው ነው የሸኙን❞ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተሸኙ ወንድማማቾች