“እናንተ ከአማራ አብራክ የወጣችሁ የደቡብ ጎንደር ዞን ምልምል ወታደሮች የዞኑን ሕዝብ ታሪክ የሚመጥን ገድል መፈጸም ይጠበቅባችኋል” የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ

245
ደብረታቦር፡ መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለዘላለም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች ተብሎ የሚነገርላት በምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች ታማኝና ቆራጥ ልጆች እያሏት ባንዳና ባዳ እንደተመኘው የሚቀልድባት ሀገር አይደለችም። ሊያፈራርሷት ቢሞክሩም በጀግኖች ልጆቿ ክንድ ራሳቸው ይፈርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትደፈርም።
የሀገሪቱ ጋሻ ከሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ የክልሎች ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና የአካባቢው ማኅበረሰብ ጠላትን እየቀበረ “ኢትዮጵያ ዘላለም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች” የሚለውን ሀሳብ በተግባር አሳይተዋል፣ እያሳዩም ይገኛሉ። ወጣቱ ዛሬም “ሀገሬ አለሁልሽ” በማለት ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል በየአቅጣጫው በነቂስ እየተመመ ይገኛል።
የወጣቶቹ ዓላማ ታላቅ ተልዕኮን ያነገበ ነው። ዛሬ ባንዳነቱን በተግባር ያረጋገጠው ወራሪውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን እና ቅጥረኞቹን ከመደምሰስ ጀምሮ ሌሎች ጠላቶችን ለማንበርከክ ወኔ ሰንቀው ነው ወጣቶቹ ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እየተመሙ የሚገኙት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶችም የሀገር አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል። ወደ ዞናቸው የገባውን ወራሪ ከመቅጣት ጀምሮ ሌሎች ጠላቶችን ለመፋለም በነቂስ ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቀላቅለዋል።
የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የዞኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የወጣቶቹ ወላጅና ቤተሰቦች ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የተቀላቀሉ ልጆቻቸውን በደስታ ሸኝተዋል።
ወጣት ታድለው ሽባባው የመጣው ከፎገራ ወረዳ ነው። “መኖርም ሆነ ሠርቶ መለወጥ፣ ማጌጥ፣ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚቻለው፣ ሀገር ስትኖር ብቻ ነው” ያለው ወጣቱ የሀገሩን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀሉን ተናግሯል።
ወጣቱ “ጠላት እቤታችን ድረስ መጥቶ እንዲያጠፋን መፍቀድ የለብንም” ነው ያለው። በመሆኑም ሌሎች ወንድምና እህት የሆኑ የሀገሪቱ ወጣቶችም ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል የእሱን ዓላማ ሊጋሩ እንደሚገባ ነው የተናገረው።
ከእብናት ወረዳ የመጣችው ምልምል ወታደር ሃይማኖት ጳውሎስ “አሸባሪው ቡድን ነፍሰጡር እናቶችን ሳይቀር አሰልፎ እኛን እየዘረፈና እየገደለ እኔ እንዴት ችዬ ቤቴ ልቀመጥ?” ብላለች። የወገኔን በደል ተቀምጬ ማየት አልፈልግም ነው ያለችው። ከወንዶች እኩል በመሰለፍ ጠላትን ለመደምሰስ ቆርጣ ለመታገል እንዳቀደች ተናግራለች።
ኢትዮጵያ የተቃጣባትን አደጋ ለመቀልበስ ያለፆታ ልዩነት ሁሉም ሊረባረብና ሊዘምት እንደሚገባ ነው የተናገረችው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የተቀላቀላችሁ የዞናችን ወጣቶች በእናንተ ኮርተንባችኋል ብለዋል። “ልጆቻችሁን የሸኛችሁ ቤተሰቦችና ጓደኞች ልጆቻችሁ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የቆረጡ ስለሆነ ደስ ሊላችሁ ይገባል” ነው ያሉት።
በዛሬ ቀን ሽኝት የሚደረግላችሁ ምልምል ወታደሮች ሀገራችሁ በጭንቅ ውስጥ ሆና ልታድኗት መከላከያን በመቀላቀላችሁ የታደላችሁ እና የተለያችሁ በመሆናችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው “እናንተ ከአማራ አብራክ የወጣችሁ የደቡብ ጎንደር ዞን ልጆች የሆናችሁ የዞኑን ሕዝብ ታሪክ የሚመጥን ገድል መፈጸም ይጠበቅባችኋል” በማለት አስገንዝበዋል።
አቶ ቀለመወርቅ ምልምል ወታደሮች በማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ተገቢውን ስልጠና በመውሰድ ጠንካራ ወታደራዊ አቋም ይዛችሁ ሀገራችሁ የሰጠቻችሁን ተልዕኮ በብቃት እንደምትወጡ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል። ታሪካዊ ጀብድ በመፈጸም የአባቶቻችሁን ታሪክ መድገም ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
“በሚሰጣችሁ ስልጠና ያላወቃችሁትን ሁሉ ለማወቅ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መላመድ እና ማወቅ ይኖርባችኋል” ብለዋል።
የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢያስቡም ኢትዮጵያ እናንተን መሰል ጀግኖች ልጆች ስላሏት ምኞታቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከደብረ ታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ መስከረም 10/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleየህልውና ዘመቻዉ በሚጠይቀው መጠን በቂ ሃብት እየተሰበሰበ አለመሆኑን የአማራ ክልል ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡