ኤጀንሲው በሀገር ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉና ያልተፈቀዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መያዙን ገለጸ።

252
አዲስ አበባ፡ መስከረም 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ያልተፈቀዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የቴሌኮም ማጭበርበሪያ /ፍራዉድ/ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ መያዙን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ገለጸ።
ኤጀንሲዉ በ2013 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ስምንት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ዉስጥ ሊገቡ ሲሉ የያዘ ሲሆን በሀገር ደረጃ ሊያደርስ የነበረዉን ከ19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳን መቻሉን በኤጀንሲዉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊዉ አቶ እሸቱ ቡሬሳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት የደኅንነት ስጋታቸዉ ከፍተኛ የሆኑ በ14 ድርጅቶች ስም የመጡ 49 ድሮኖችና የስለላ ካሜራዎች ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ መከልከላቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች መካከልም የቴሌኮም ፍራዉድ መፈጸም የሚያስችል (sim box) ፣ ስፓይ ካሜራ፣ ሳተላይት ስልክ፣ ድሮን ፣ የመገናኛ ሬዲዮ፣ ወታደራዊ ባይነኩላር እና የቅኝት መሳሪያዎች፣ ለሰቪላዊና ወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ጂፒኤሶች፣ ድብቅ የድምፅ መቅጃ ማይክራፎኖች፣ ዱዋል ባንድ ራዉተር፣ Transmitters (fm) እና vsat ይገኙበታል ተብሏል፡፡
በመሆኑም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት አስመጭዎች ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ዓይነት በመለየት ማስመጣት እንደሚገባቸዉ ኃላፊዉ ማሳሰባቸውን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ኤጀንሲው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና ከሀገር ውጪ የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች፣ የመረጃ ማነፍነፊያዎችና የጥቃት መፈጸሚያ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ደኅንነት ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ የመከላከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ደጎች ለልጆች እንጎቻ ይሰጣሉ፣ ክፉዎች ለመሞቻቸው ቦንብ ያስቀምጣሉ❞
Next article“ታላቁ ጉልበታችን ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ