❝ደጎች ለልጆች እንጎቻ ይሰጣሉ፣ ክፉዎች ለመሞቻቸው ቦንብ ያስቀምጣሉ❞

224
ደባርቅ: መስከረም 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ አዝናባቸዋለች፣ አፍራባቸዋለች፣ የኢትዮጵያዊነት ክብር፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ የኢትዮጵያን ምስጢር አያውቁምና ኢትዮጵያውያንን በደሉ፣ አንድነትን ደብቀው መለያያ ፈልገው ከፋፈሉ፣ ከኢትዮጵያ ጠላቶች በጋራ አበሩ፣ ኢትዮጵያን ለሚወጓት መንገድ መሩ፣ ከጠላቶቿ ጋር ጦር ሰደሩ።
ኢትዮጵያ እያኖረቻቸው፣ እየመገበቻቸው፣ ጡቷን ይነክሳሉ፣ እጇን ይቆርጣሉ። በእናት ሀገራቸው በደል ፈፅመዋል፣ እናታቸውን ክደዋል፣ የእናታቸውን ልጆች አርደዋል፣ ንብረታቸውን ዘርፈዋል። ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ክብሯን ለማርከስ፣ ማዕረጓን ለማንኳሰስ፣ ኢትዮጵያዊያንን ለማሳነስ ያልሠራው ሥራ አልነበረም። ኢትዮጵያን የሚውዱ ሁሉ ጠላቶቹ፣ ኢትዮጵያን የሚጠሉ ሁሉ ወዳጆቹ ናቸው።
ለኢትዮጵያ የቆመ፣ ስለ ኢትዮጵያ የሚኖር፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብር፣ ስለ ሀገር የሚዘምር ሁሉ ጠላቱ ነው አሸባሪው ትህነግ። ወራሪውና አሸባሪው ትህነግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን አብዝቶ የሚወዳትን፣ ለክብሯ ሲል የሚሞትላን አማራን አብዝቶ ይጠላል። እልፍ አማራዎችን ገድሏል፣ አካላቸውን አጉድሏል፣ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፏል፣ አውድሟል፣ ከመኖሪያ ቀያቸው፣ ከተደላደለው ርስታቸው አፈናቅሏል።
እንኳን ተጋላቢውን ጋላቢውንም በጥይት መትቶ፣ እጅ አስነስቶ የሰደደው አማራም በደሉ ሲበዛበት ትህነግን ከዙፋን አወረደው። ለዓመታት የታገሰው አማራ፣ መዋቅሩን አፈረሰው፣ ዝናውን ገረሰሰው፣ ብዙውን አፈር አለበሰው። ከአፈር የተረፉት ግን ዛሬም ከአማራው ላይ በደላቸውን መፈፀም አላቆሙም። የትግራይ ወራሪ ቡድን ዛሬም አማራን ወርሯል፣ አፈናቅሏል፣ ገድሏል፣ ሀብትና ንብረት ዘርፏል።
ወራሪውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ ከፈፀመባቸው የአማራ አካባቢዎች አንዱ ስሜን ጎንደር ነው። በስሜን ጎንደር ዞን በጀግኖች አፈሙዝ እየተለዬ ሲለቀም፣ የባሩዱን እሳት አልችለው ሲል ወደኋላ ፈረጠጠ። ታዲያ ሲፈረጥጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐንን ገድሎ ነበር የሸሸው። ንጹሐንን ከጨፈጨፈባቸው አካባቢዎች አንደኛው ደግሞ ቦዛ ነው።
በቦዛ ንጹሐንን ገድሎ፣ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፎ፣ ያልቻለውን አውድሞ ሲሄድ ንጹሐን ወደቀያቸው ሲመለሱ ይሞቱ ዘንድ የሞት ወጥመድ አጥምዶላቸው ነበር የሄደው። ከብቶች እንዲሞቱ በከብቶች ማደሪያ፣ ልጆች እንዲያልቁ በልጆች መጫዋቻ ቦንብ እየጣለ፣ ፈንጅ እያጠመደ ሮጠ።
ደጎች ለልጆች እንጎቻ ይሰጣሉ፣ክፉዎች ለመሞቻቸው ቦንብ ያስቀምጣሉ። ደጋጎቹ ለልጆች ደስታን እንጂ ሞትን አይመኙም። ክፉዎቹ ግን ልጆች ይገድሉ ዘንድ ይጥራሉ። በለጋ እድሜያቸው ይቀላሉ። ወይንም እናት አባቶቻቸውን ገድለው አሳዳጊ እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ።
ጨካኞች ልጆች እንዲያልቁ በጣሉት ቦንብ ልጃቸው ጉዳት ከደረሰባቸው እናት ጋር ተገናኝተናል። ወይዘሮ አበቡ ብርሃኔ
ይባላሉ። የሚኖሩት በቦዛ አብርሃም ነው። በወርሃ ነሐሴ አንድ ዓመት የሞላት እንቦቀቅላ ልጅ ታቅፈዋል። ልጃቸውን ዓለም ታሳያቸው ዘንድ ዓለሚቱ ብለዋታል። እውነትም ዓለም። ዓለምን የምታሳይ ደስታን የምትሰጥ፣ ሐሴትን የምትመግብ ውብ ልጅ፣ መልከ መልካም። ወይዘሮ አበቡ ቆንጆዋን ልጃቸው ታቅፈው በሆስፒታል ውስጥ ነበር ያገኘናቸው።
ሰላምታ ሰጠዃቸው። በመልካም ለዛ አፃፈውን መለሱልኝ። ከአጠገባቸው ተቀምጬ ስለ አሳለፉት ነገር ጠየኳቸው።
❝መጡ፣ እናንተን ምንም አንላችሁም፣ ያላችሁን ስጡን አሉን። ያለችው እስከምታለቅ ሰጠናቸው። ኋላ ግን አለቀብን ለእኛ። ለእኛ ሲያልቅብን ምን እንስጣችሁ እንግዲህ አልቆብን አይደል አልናቸው። እናንተ ምን ልትበሉ ነው አሉን። እኛማ ያለችውን ለእናንተ አበላን። ወደሚሄደው ሀገር መሄድ ነው እንጂ አልናቸው። ከገባችሁበት ገብታችሁ አምጥታችሁ ስጡን አሉን❞ ወይዘሮ አበቡ ያን ጊዜ እያስታወሱ በትዝታ ወደኋላ ተመለሱ። በደል እንደደረሰባቸው ነብሳቸውን እንዳስጨነቋት፣ ቤታቸውን እንዳመሷት ያስታውቃሉ። ዝም አሉ በመካከል። ከትዝታ ባሕር ዋኝተው፣ በትዝታ ጎዳና ተመላልሰው ይመጡ ዘንድ ዝም አልኳቸው።
❝እሚሸጥ የለነ ፍየሉን አረዳችሁት። አማራጩ መውጣት ነው ብለን እኛ ከቤት ወጣን። እኛ ለእነርሱ ሰጥተን ለልጆቻችን እንኳን የምንሰጠው ስናጣ ነው የወጣን። እንዳይገድሉን በሩጫ ከቤት ወጣን። ቤት ፈተሹ። ጎታን በቆመጥ እያሉ አፈረሱ። ልብሳችን ቀዳደዱ። ለአንድ ሳምንት ያክል በዋሻ ውስጥ ተቀመጥን። ከዚያ በቆላው ዘመድ እንቀበላችሁ ብሎን ወደ ቆላው ሄድን። ምን አልያዝንም ይህችን ነጠላ ብቻ ነው ይዤ የሄድኩት❞ አሉኝ ወይዘሮ አበቡ ከላያቸው ላይ የደረቧትን ልታልቅ የተቃረበች ነጠላ እያሳዩኝ።
ወይዘሮ አበቡ የታናሿን ልጃቸውን ታላላቅ ወንድሞችና እህቶች ይዘው ይጠለሉ ዘንድ ከዋሻ ወጥተው ወደ ቆላው ወረዱ። በቆላው ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋርም ተገናኙ። በዚያውም ተቀመጡ።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በታላቅ ጀግንነት ጠላትን እየመቱ ነበርና በቦዛ የገባውን አሸባሪ ቡድን አሳምረው ቀጠቀጡት፣ በጥይት ጅራፍ ገረፉት፣ አቆላልፈው ረፈረፉት። ከቦዛና ከሌሎች አካባቢዎችም ተለቃቅሞ ወጣ። ይህን የሰሙት እነ ወይዘሮ አበቡ ቀያቸው ናፍቋቸዋልና ወደ ቀያቸው ተመለሱ።
❝ከረጋገጧት አዝመራችንን የተረፈችውን ለማረምና ለቀለብ ለማትረፍ መጥተን ከቤታችን ገባን። ከቤታችን የቀረን ነገር የለም። እቃውን ስብርብር አድርገው ወለሊቱን ሙሊት አድርገዋት ቆዩን። እሳታችን አንደን ቁጭ አልን። ለነብሴ ያለ ወገን ሰጠን እሷን እየበላን ተቀመጥን❞ አራሾቹና አጉራሾቹ በግፈኞች ተዘርፈው ለልጆቻቸው የሚሰጡት እስኪያጡ ድረስ ተቸገሩ። ይህም ይሁን ቀኑን ያሳልፉታል አዝመራውም ይደርሳል። ችግሩም ይታለፋል ብለው ዝም አሉ።
ከበደል ላይ በደል ሲጨመር ለቤታቸው ሌላ ችግር መጣ። ወይዘሮ አበቡ ታናሿ ልጃቸውን በቤታቸው እየተዉ ሥራ መሥራት ጀምረዋል። ጠላት ተጠራርጎ ስለወጣ ልጃቸውን ምንም ያገኝብኛል ብለው አልሰጉም።
❝ውኃ ልቀዳ ከታላቅ ወንድሟ ጋር ቆዩኝ ብዬ ትቻት ሄድኩ። እንደሄድኩ ጭንቅ አለኝ። የሚፈነዳ ድምፅ ስለሰማሁ ልጆቼን ጭፍልቅ አድርገዋቸው ሄዱ ብዬ ተጨነኩ። ትላልቆቹ እሪሪሪ… አሉ። ስሄድ ጨቅላይቱ በደም አላባ ዋጥ ብላለች❞ እናት ይህን ሲያዩ ተንሰፈሰፉ። በጤና አስቀምጠዋት የሄዱት ተወዳጅ ልጅ ሲመለሱ በደም ተዘፍቃ ስትንሰፈሰፍ አግኝተዋታልና።
❝ከደጃፍ የምናበስልበት ምድጃ ነበር ድንጋይ ግጥም አድርገን ትተነው ነበር። ከእሷ ውስጥ አስቀምጠዋት ሄደው ኖሯል። ታዲያ ጨቅላይቱ እየዳኸች ሄዳ ነው። ያወጣችው❞ ከልቧ ክፋት ያልፈጠረባት ታናሿ ዓለሚቱ እየተሳበች ሄዳ ለሞት የተቀመጠውን ቦንብ ነካችው። አብረዋት ይጫወቱ የነበሩ ሕጻናትም ከድንጋይ ጋር አጋጩት። ቦንቡ መጫወቻ የመሰላት ታናሿ ልጅ በየዋህ ልቧ ባልጠናው እጇ ሳበቻት። ለመግደል ዝግጁ ነበርና ቦንቡ ፈነዳ።
ሕፃናት በድንጋጤ ወደቁ። እሪታው ቀለጠ። እንቦቀቅለዋ ዓለሚቱ እጇ በደም ተዘፍቋል። ሕፃናቱ ተረበሹ። እናት አምርረው አለቀሱ። ዳሩ ፈጣሪ የከለላትን ነብስ የሚገድል የለምና የፈነዳው ቦንብ ሚጣዬን አቁስሎ ሌሎችን ምን ሳይነካቸው ቀረ። የሞት ወጥመድ በፈጣሪ እርዳታ አለፈ። የሚጣ ቁስል ግን መንደሩን ረበሸው። ያያትን አሳዘነው። ከሞት የተረፈችውን ሚጣን ይዘው ወደ ሆስፒታል ሄዱ።
ወይዘሮ አበቡ ልጃቸው የገጠማትን አደጋና የተረፈችበትን መንገድ ሲያስቡ ይገረማሉ። ለእርሳቸው ብሏት፣ ለተዓምር ቢያስቀምጣት እንጂ እርሷም ከእርሷ ጋር ያሉትም ባለቁ ነበር። ፈጣሪ ግን ከለላቸው። ከሞት መንጋጋ አወጣቸው።
❝አድጋ እንዳትጠቅም ጠላት ቢገፋት
ቸሩ ፈጣሪ ከሞት መንጋጋ ፈልቅቆ አወጣት❞ ታናሿ ዓለሚቱ ጠላት እንዳታድግ ቢመኝም፣ የመሞቻዋን ወጥመድ ቢያጠምድም፣ ፈጣሪ ግን አተረፋት። ለወላጆቿ እንደ ስሟ ዓለም ትሆን ዘንድ እንድታድግ ፈቀደላት።
ወራሪው ቡድን ፍየሎቻቸውን አርደው እንደበሉባቸውም ነግረውናል። ❝ቤታችን ውስጥ ደሮም አልተውልን፣ እንዳሻው መቅሪያቸው ከሆነ። የአሁኑ ረሃብ ረሃብ ነው። የተገኘውን ይዘን። እንደ ሀገር ቁጭ አልነ❞ ነው ያሉት።
የአካባቢው ሰው ችግር ውስጥ መውደቁን እና ድጋፍ እንደሚያሸውም ነግረውናል። ማስተማሪያም አታድርገኝ ማስተማሪያም አትንሳኝ እንደተባለ የእኔ ልጅ የደረሰባትን ሌላው እንዳይደርስበት እናቶች ልጆቻቸውን ይጠንቀቁም ብለዋል። ሚጣዬም በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ተሰጥቷት በመልካም ጤንነት ነው ያገኘኋት። የጨካኞች ግፍ ቢያሳዝነኝም ሞት ተደግሶባት የነበረው ታናሿ ልጅ ከሞት ተርፋ ስለአየኋት ደስ ብሎኛል።
እንቦቀቅላ ልጆች እንኳን እንዲያድጉ የማይፈልግ ጨካኝ ቡድን አብራክን እየነጠቀ፣ መንደርን እያጠፋ፣ በደል እየፈጸመ በቃህ ብሎ መነሳት፣ ተከታትሎ ማጥፋት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleወልቃይት ጠገዴ ለጠላት ምኅረት የላትም፡፡
Next articleኤጀንሲው በሀገር ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉና ያልተፈቀዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መያዙን ገለጸ።