“እኔ በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም” ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ

274
ባሕር ዳር፡ መስከረም 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ፣ ለመርህ፣ ለዓላማ እና ለሰብዓዊ መብት ትግል የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡ ከምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ እስከ ካናዳ ለደረሰ ኢትዮጵያዊነት፣ ከሜክሲኮ እስከ ጃፓን ለተከፈለ ተጋድሎ የሚውል ክብር እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ለፊት ለታየ ኢትዮጵያዊ ምስክርነት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አበርክቷል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ሰው ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ለክብር ዶክትሬት ማዕረግ አብቅቷል፡፡ ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ ሰው ብቻ ሳይሆን ሀገርም ጭምር ነውና፡፡ ከጋንቤላ አብራክ፤ ከኢትዮጵያ ማሕጸን የበቀለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የማኅበረሰብ አንቂ እና በጎ አድራጊው ሰው ኦባንግ ሜቶ ለነፃ የትምህርት እድል ወደካናዳ ያቀናው ገና በ19 ዓመቱ አካባቢ ነበር፡፡
በትምህርት እና ሥራ በውጭ ሀገራት የቆየው ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ በአካል አውሮፓ ውስጥ ቢሆንም በመንፈስ ግን ሀገሩን አልረሳም ነበር፡፡ በልጅነት መውጣቱ፣ የተደላደለ ሕይዎት መምራቱ እና ቤተሰብ መመስረቱ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቹን አላስረሳውም ነበርና ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ወደሀገሩ ተመልሶም በጋምቤላ እና በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ የበጎ አድራጎት እና ማኅበረሰብ አገልግሎት መስኮች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
በጭፍጨፋ ገብቶ በሕዝብ አመፅ የወጣው የያኔው የሀገረ መንግሥት መሪ የአሁኑ አሸባሪ ትህነግ በአኝዋክ ብሔር ተወላጆች ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የዚህን በጎ ሰው ቅስም ክፉኛ ሰበረው፡፡ የሕይዎት ዘመን ጥሪውም ከበጎ አድራጎት ሥራዎች ወደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ተሸጋገረ፡፡
ከነገረ ቀደም ወደ ካናዳ ያቀናው ለትምህርት፣ የተማረውም ፖለቲካል ሳይንስ እንደነበር ስናስታውስ የሕይዎት መስመሩ ጥሪ በዚህ መንገድ ቢቃኝ ብዙም አያስገርምም፡፡
ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዓለም የሰብዓዊ መብት አድቮኬሲ መስመርን ተከትሎ ከዘር፣ ከቀለም፣ ከብሔር፣ ከቋንቋ እና ከማንነት በላይ ሰው መሆን ይበልጣል ሲል በዓለም አደባባይ ስለፍትሕ እና ስለነፃነት አበክሮ አስተጋባ፡፡
የመሪዎችን ግልምጫ እና የጋሻ አጃግሬዎቻቸውን ተፅኖ ሳይፈራ እና ሳይሸሽ ለመርህ እና ለእውነት ተግቶ ታገለ፡፡
“ሁሉም እንደሀገር ነፃ ካልወጣ ግለሰቦች ነፃ አይወጡም” በሚለው መርሁ የሚታወቀው ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ 10 የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ እንዲካሄዱ አድርጓል፡፡
በጃፓን ታስረው የነበሩ 17 ኢትዮጵያዊያን እና በሜክሲኮ ለወራት ታስረው የነበሩ 19 ኢትዮጵያዊያን እንዲለቀቁ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ያደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለክብር ካበቁት አበርክቶዎቹ መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡
“የአኝዋኩ ጭፍጨፋ ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚያደርገውን ትግል በበቀል ወይስ ከዚያ በተሻለ አማራጭ ላድርገው የሚለውን ጥያቄ ደጋግሜ አስቤበት ነበር” የሚለው ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ በኢትዮጵያ ጠላቶች መንገድ መጓዝ ከእነርሱ አለመሻል ነውና ከበቀል ይልቅ አሁን የያዝኩትን አማራጭ የወሰንኩት አስቤ ነው ይላል፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነት፣ ዘረኝነት፣ ቋንቋ እና ሌሎች ማንነቶቻችን ሳይሆኑ ሰው ያሰኙን ሰው ለመሆን መትጋት እና መታገል ነው ይላል፡፡
ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ በንግግሩ “የእኔ ተስፋ የአሁኖቹ የሀገሪቱ መሪዎች ሳይሆኑ የአሁኖቹ ተመራቂዎች እና የነገይቱ የሀገሪቱ ተረካቢዎች ናችሁ” ሰው ሁኑ፣ ሰው ብላችሁ ተነሱ፣ ለዓለም የሰው ልጆች መብት መከበር እና እኩልነት ተግታችሁ ሥሩ ብሏል፡፡
አሁን ቆመን የምንነጋገርባት የዓባይ ወንዝ አብራክ ባሕር ዳር ከገጠመን የሕልውና ሥጋት ጋር ጦርነት የምንገጥምበት ቦታ ብዙም ሩቅ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የምንዋጋው ከጠላት ጋር ሳይሆን ከወንድም ሕዝብ ጋር ነው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው መሪዎቻችን የሄዱበት እና የመረጡት የልዩነት መንገድ ኢትዮጵያዊነታቸውን አስረስቶ ጠባብ ብሔርተኝነትን ስላለማመዳቸው ብቻ ነው፡፡ ከእንደዚህ አይነቱ መንገድ የምንመለስበት እና ኢትዮጵያ ብለን የምንነሳበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ “እኔ በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም” ነው ያለው፡፡
አሜሪካ እንደ ሀገር ሳትታወቅ ኢትዮጵያ ጥንተ ሀገር ነበረች ያለው ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ በርሃብ የምንጠበሰው፣ በድህነት የምንሰቃየው እና ማንም እንደፈለገ ሊያዘን የሚፈልገው ድሃ ስለሆንን ነው ብሏል፡፡ ድህነታችንም ከሀብት ማጣት ሳይሆን ከትብብር ማነስ እና አብሮ ካለመቆም እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሁላችሁም የእኔ አካል ናችሁ፤ እኔም የእያንዳንዳችሁ አካል ነኝ፡፡ ማንነታችንም ከተደረበልን ቋንቋ እና ብሔር በላይ ነውና አብረን ለመቆም ከአሁኑ የተሻለ ጊዜ የለም ብለዋል፡፡
“ምዕራባዊያኑ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚጠቀሙት እኛን ራሳችንን በመሆኑ ሀገራችን ለመታደግ በጋራ እንቁም” ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም ይህ የክብር ዶክትሬት የተበረከተው ለኦባንግ ሜቶ ሳይሆን ለመርህ፣ ለዓላማ እና ለኢትዮጵያ ነው ያለው ክቡር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ ይህ እንዲሆን ለፈቀደ ፈጣሪ፣ ከጎኔ ለነበሩ እና ለተባበሩኝ ሁሉ ይሁን ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየምሥራቅ አማራ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እየመከሩ ነው።
Next articleአሸባሪው ትህነግ ከባድ መሳሪያ በመጠቀም በአንድ ቀን ከ600 በላይ ንጹሐንን እንደጨፈጨፈ ከቆቦ ከተማና ዙሪያዋ ተፈናቅለው በዞብል የተጠለሉ የዓይን እማኞች ገለጹ።