❝በቅርቡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የድል ብሥራት እናሰማለን❞ የምእራብ እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል መሠለ መሠረት

822
ደባርቅ: መስከረም 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥትና የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች በማይጠብሪ ግንባር የሚገኘውን ሠራዊት አበረታተዋል።
በግንባሩ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በታሪኩ ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ፣ ኢትዮጵያን ነክቶ ጤና ያገኘ የለም፣ ጣልያን ሞክራለች፣ ከኢትዮጵያ ከወጣች በኋላ የድሮዋ ጣልያን አልሆነችም፣ ሱዳንም ነክታለች የድሮዋ ሱዳን መሆን አልቻለችም ነው ያሉት።
ከፈጣሪ በታች የኢትዮጵያ ወኪል የመከላከያ ሠራዊት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀግና እጥረት የሌለባት ሀገር ናት፤ የኢትዮጵያ አርሶአደር እህል ማምረት እንደማይሰለች ሁሉ ኢትዮጵያም ጀግና ከመፍጠር አትቦዝንም ነው ያሉት።
❝ጠላት ኢትዮጵያን አያውቃትም፤ ኢትዮጵያን ቢያውቃት አይነካትም ነበር፤ ለዛም ነው ተንደርድሮ የገባው፣ ቅስሙንም አቅሙንም እንዳይነሳ አድርገን እንሰብረዋለን❞ ሲሉ ገልጸዋል።
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አቅሙንም እንደማያውቅ ነው የተናገሩት።
አሸባሪው ትህነግ እየገፋ ያለው ተራራ ነው፤ ትዕግሥት የጀግና ጠባይ ነው፣ እናንተ አንበሶች፤ ጠላቶቻችን ደግሞ አይጦች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ጠላት ገብቶ አይወጣም፤ እስካሁንም አልወጣም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ልብ የሚያርዱ ጀግኖች እንዳሏት በማወቃችን እጅግ ደስተኞች ነንም ብለዋል።
የብልጽግና ጽሕፈት ቤት የሕዝብና ውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አማካሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተዓምር መሥራት የቻላችሁ ጀግኖችን በማየታችን ደስተኞች ነን፤ ከእናንተ ጋር መጥተን ብንሰዋም አይቆጨንም ነው ያሉት።
መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ክብር የታየበት ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል። ምንም ሳያግዳችሁ ለኢትዮጵያ ክብር በመቆማችሁ ክብር ይገባችኋልም ብለዋል። የኢትዮጵያን ልክ ማወቅ የፈለገ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማዬት አለበትም ነው ያሉት።
❝ለኢትዮጵያ ክብር ለምትዋደቁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ኢትዮጵያ ለዘላለም ታመሰግናችኋለች፤ ለኢትዮጵያ ስንል መስዋእት እንሆናለን ያላችሁ ወታደሮች ብቻ ሳትሆኑ አንድነት እና ኢትዮጵያዊነትን የምታስተምሩ አስተማሪዎች ናችሁ❞ ብለዋቸዋል።
ጠላት እንደተቀበረ አውቆታል፣ እንደቀበራችሁት ደግሞ አይተናል፣ ኢትዮጵያውያንን ነክቶ እንደሚቀበር ለውጭ ጠላትም ትምህርት ሰጥታችኋል፣ የውስጥ ጠላቶችም ተስፋቸውን ይቁረጡ፤ ለኢትዮጵያ ክፉ ያሰቡ ሁሉ ይቀበራሉ ነው ያሉት።
የምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል መሠለ መሠረት እኛን ለማዬት ስለመጣችሁ እናመስግናለን፤ ስንቅ ነው የሰጣችሁን ብለዋል። ❝የቀረ ጥቂት ኃይል አለ፤ እርሱንም ደምስሰን በቅርቡ ለእናንተም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የድል ብሥራት እናሰማለን❞ ሲሉ ገልጸዋል።
❝አደራ ሰጥታችሁናል። አደራችሁን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን፤ አኩርታችሁናል እኛም እናኮራችኋለን ነው❞ ያሉት። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው በወሎ ግንባር ለተፈናቀሉ ዜጎች 100 ሚሊየን ብር መደቡ፡፡
Next article“ከሽብር ቡድኑ ነፃ በሚሆኑ አካባቢዎች ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት በአፋጣኝ ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል” የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር