በወረዳው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት እንደሚያቋቁም የዳባት ወረዳ አስተዳደር ገለጸ።

105
ደባርቅ: መስከረም 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት እና የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ግፍ የፈፀመበትን የጭና ቀበሌን ተመልክተዋል።
በሥፍራው ተገኝተው ለተመለከቱት የሥራ ኃላፊዎች የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን ገለፃ አድርገውላቸዋል። በገለጻቸውም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በዞኑ ከሰኔ 30/2013 ዓ.ም ጀምሮ ወረራ መፈፀሙን ነው የተናገሩት። ከዛሪማ በመነሳት በእግሩ በመውጣት ወደ ቦዛና ጭና መውጣቱን ተናግረዋል። ወራሪው ቡድን በየደረሰበት እየተመታ፣ እያለቀ፣ ኅይል እየጨመረ መጥቶ ጭና ላይ ሲደርስ መደምሰሱን ነው የተናገሩት ።
አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን እየተመታ አብዛኛው ባለበት መቅረቱንም ገልጸዋል። በዳባት ወረዳ ጭናን በመቁረጥ ከቅማንት ፅንፈኛ ቡድን ጋር በመገናኘት እና ጎንደርን መቆጣጠር ዓልሞ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የወራሪውን ቡድን ዓላማ ለማምከን የታጠቀም ያልታጠቀም ኃይል ባደረገው ተጋድሎ መደምሰሱን ነው የተናገሩት።
ወራሪው ቡድን በአካባቢው በቆየባቸው ቀናት እንስሳትን ገድሏል፣ ንጹሐንን ጨፍጭፏል፣ በጭና ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ተገድለዋልም ነው ያሉት።
ከሃይማኖት አባቶች ላይ ጥቃት አይፈፅምም ሲባል ለይቶ መግደሉንም ተናግረዋል። የጠላት ቡድን ሸሽቶ ሲሮጥ ገደል እየገባ ማለቁንም ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ላገኘው ድል የሕዝቡ ደጀንነት ትልቅ ድርሻ እንደነበረውም ተናግረዋል። የስኬቱ ምስጢር የሕዝቡ ደጀንነት ነውም ብለዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በመወጋት፣ ሥንቅ በማቀበልና መረጃ በማቀበል አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት። በጭና ሲመታ ከኋላ የነበረው በነብስ አውጭኝ መፈርጠጡንም ጠቅሰዋል።
ጠላት የራሱን ሙቶች በአርሶ አደር ቤት ውስጥና በጓሯ መቅበሩንም ተናግረዋል።
አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡደን ዓይነ ስውራንና ሕጻናትን ጭምር የገደለ አረመኔ መሆኑንም ገልፀውላቸዋል።
የዳባት ወረዳ አስተዳዳሪ ሰውነት ውባለም ወራሪው ቡድን በወረዳው ከፍተኛ በደል መፈፀሙን ተናግረዋል። ድል እንደማይቀናቸው ሲያውቁ በንጹሐን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን ነው የገለፁት። በየትኛውም ሀገር ያልተደረገ በደል በጭና ላይ ተፈፅሟልም ነው ያሉት።
ነዋሪዎችን እያወያዬን ወደ ቀያቸው እየመለስን ነውም ብለዋል። መንግሥትና የተራድኦ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
❝ማኅበረሰባችን እናረጋጋለን፣ በዘላቂነት እናቋቁማለንም❞ ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ አሁን እየተደረገለት ካለው ድጋፍ በላይ ድጋፍ እንደሚሻ የተናገሩት አስተዳዳሪው ከሚመለከተው አካል ጋር እየተገናኘን ድጋፍ እናደርጋለንም ብለዋል።
ነዋሪዎችም አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ያደረሰብን በደል እንደዚህ ነው ተብሎ የሚገለጽ አይደለም ነው ያሉት። አጥፍተህ ጥፋ የሚል ብሂል ይዘው ጭና ድረስ መጥተው በሴትና ወንድ ተጋድሎ ተደምስሰዋል ነው ያሉት።
ጀግናው ሠራዊት የሠራው ተጋድሎ የሚደነቅ ነውም ብለዋል። ደካሞችንና እናቶችን ሲያታልሉ ከርመው መሸነፋቸውን ሲያረጋግጡ ገድለዋቸው መሄዳቸውንም ተናግረዋል። መሸነፋቸውን ሲያረጋግጡ መኖሪያ ቤቶችን በጥይት እየተመቱ መሄዳቸውንም ገልጸዋል። አምስት ቀንና ሌት ያደረጉት ተጋድሎ ሳይሳካ ሬሳ ሆነው ቀርተዋልም ብለዋል። ንጹሐን ሙተዋል፣ ንብረት አልተረፈም፣ በሰፊው ልታስቡን ይገባል ነው ያሉት።
የቤተክርስቲያን ንብረት ማውደማቸውናና መዝረፋቸውንም ገልጸዋል። ❝ሰው የተፈጠረው ለሞት ነው፤ በሞታችን አንቆጭም ጠላቶቻችን አንድነታችን አጠናክረው ሄደዋልም❞ ነው ያሉት።
ወገኖቻችን የሞቱት ሲሰርቁ ሲዘርፉ አይደለም፣ የሞቱት በጀግንነት ነው፣ ወገኖቻችን ሞተው ብንሸነፍ ኖሮ ይቆጨን ነበር፤ አሁን ግን በድል ተገናኝተናል ደስተኞች ነንም ነው ያሉት። ለወገን ጦርና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል። እየተደረገው ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት ነዋሪዎቹ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ጭና በሁለት መልኩ ታሪኳ ተፅፎ ይኖራል፤ አንደኛ የክፉውን የወያኔን ግፍ በመናገር ሁለተኛ የጭናን ሕዝብ ጀግንነት በመናገር❞ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
Next articleአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የሀገር ሰላም ስጋት እንዳይሆን እየቀበሩት መሆኑን በወሎ ግንባር የተሰለፉ የጦር መኮንኖችና የሠራዊት አባላት ገለጹ፡፡