
መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና መታደግ እንዳለባቸው በወልቃይት ጠገዴ ግዳጅ የተሰማሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ አቅርበዋል። መከላከያ የሀገር ፍቅር ስሜት በተግባር የሚታይበት የተከበረ ተቋም እንደሆነም የሠራዊት አባላቱ አንስተዋል።
ለሚወዱት ከነፍስ በላይ ምን ሊሰጥ ይችላል? ወታደሮች ከራሳቸው አብልጠው ለሚወዷት ሀገራቸው መተኪያ የሌላት አንድያ ነፍሳቸውን ያለ ስስት እየሰጡ ነው። ውትድርና ስለ ሀገር ፍቅር ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ለክብር፣ ለነጻነት እና ለሉዓላዊነት መከበር በቁርጠኝነት፣ በጀግንነት እና በጽናት መታገል ነው።
የውትድርና ሙያ ለሀገር፣ ለፍቅር፣ ለሉዓላዊነት፣ ለክብር እና ለኢትዮጵያዊ አንድነት መሰጠት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ ተፈትሎ የተሸመነ ሕብር የአንድነት ቃል ኪዳን ነው።
ወታደር መለዮውን የሚወድ ለሀገሩ ክብር ውድ የሆነችውን ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ቆራጥ ዜጋ ነው። ጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ያጋጠሙ ከባድ ፈተናዎች ያለፉት ሀገራቸውን ባስቀደሙ ወታደሮች ደምና አጥንት ነው።
የኢትዮጵያ ሠራዊት የሀገሩ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያስቻለ እና ድንበር ተሻጋሪ የሰላም ማስከበር የጀግንነት ታሪክ ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል።
የሠራዊት አባላት እንደሚሉት መከላከያ የመሰዋእትነት ተቋም ብቻ አይደለም ዕውቀት የሚገበይበት አንጋፋ የትምህርት ተቋም ጭምር እንጅ። ሠራዊቱን የተቀላቀሉት ወጣቶች አዳዲስ ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ጠንካራ የሀገር ፍቅር ስሜት ከመገንባት ባለፈ ከሰው ጋር የመኖር፣ በቀላሉ የመግባባት፣ የመረዳዳት እንዲሁም ፈተናን ተቋቁሞ በቀላሉ የማለፍ ጥበብ እና አቅምን አዳብረዋል።
ከግዳጅ ጎን ለጎን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ በማንሳትም ተቋሙ ዘርፈ ብዙ የሙያ ስልጠና የሚገኝበት መሆኑ ለሠራዊት አባላቱ ተጨማሪ ዕድል እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ።
ሠራዊቱን ተቀላቅሎ ለሀገር ክብር መታገል ትልቅ ክብር መሆኑን በመረዳት በራሳቸው ተነሳሽነት የተቀላቀሉ የሠራዊት አባላቱ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢያጋጥማቸውም ስለ ውድ ሀገራቸው መስዋእትነት መክፈላቸው ከችግሩ የገዘፈ ትልቁ የኩራት ምንጫቸው እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን ከውስጥና ከውጪ ጠላት ለመታደግ መመረጣቸው እንዳኮራቸው አንስተዋል።
በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ሠርቶ ማግኘት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ብቻ በመሆኑ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ፈተናዎችን በጽናት አልፈው ሀገራቸውን እንደሚያስከብሩ ነው የሠራዊት አባላቱ የተናገሩት።
ያለ ሀገር መኖር ስለማይቻል ሁሉም ቅድሚያ ለሀገር መኖርን ሊያስቀድም እንደሚገባ አባላቱ ገልጸዋል።
ለዚህም ወጣቶች ተቋሙን በመቀላቀል፣ በመሰልጠን እና ግንባር በመሰለፍ ለሀገራቸው ክብር የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል። በተለይ በዚህ ወቅት ሠራዊቱን መቀላቀል የግድ የሚልበት ነው ያሉት የሠራዊት አባላቱ ወጣቶች ሀገርን ለማዳን ተቋሙን በመቀላቀል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m