
መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገው የሠራዊት ግንባታ ሂደት ዓላማው አሸባሪው ሕወሓትን ማሸነፍ እንዳልሆነና ይልቁንም ዝግጅቱ እነሡን ለሚጋልቧቸው ኀይሎች እንደሆነ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
የቡልቡላ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ በመሰረታዊ ውትድርና ያሰለጠናቸውን ወታደሮች የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት አስመርቋል።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ባደረጉት ንግግር፤ ❝የእኛ ዝግጅት ለጁንታው አይደለም፤ ይልቁንም እነሱን ለሚጋልቧቸው ገዢዎቻቸው ነው❞ ብለዋል፡፡
ሌተናል ጄነራል ባጫ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም መሰል ችግሮች ሲያጋጥሟት እንደነበር ገልጸው፤ በእነዚህ ጊዜያት ግን ባንዳዎች ሀገርን በማስጠቃት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

በሁለቱም የጣሊያን ወረራዎች ወቅት ባንዶች ሀገርን በመውጋት ድርሻቸው ብዙ እንደነበር የተናገሩት ሌተናል ጄነራሉ፤ በሶማሌ ወረራ ወቅትም የዛሬው አሸባሪ ሕወሓት የሶማሌን ወረራ ከማውገዝ ይልቅ ለጠላት ወግኖ ነበር ብለዋል፡፡
ሀገርን ማዳን የሚቻለው በቅብብል ነው ያሉት ሌተናል ጄነራል ባጫ፤ ይህ ትውልድም ባንዳውን ሕወሓትን ማስወገድ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በዚህ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ዓላማ አላት ያሉት ሌተናል ጄነራል ባጫ፤ ❝ሀገራችንን አታፍርሱ የሚል ፍትሐዊ ዓላማ የተቀበለ 110 ሚሊየን ሕዝብ አለን፤ ድሆች ብንሆንም የሎጀስቲክ ምንጭ የሆነ ሕዝብ አለን❞ ሲሉ ተናግረዋል።
❝ተመራቂዎች ድል አድራጊ የሆነውን ሠራዊት ተቀላቅላችሁ በቅርቡ ድል እንደምታበስሩ ተስፋ አለኝ❞ ብለዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ