
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2012 ዓ/ም (አብመድ) የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
“ዮዮ ግፋታ” ማለት እንኳን ለወላይታ የዘመን መለወጫ በሰላም አደረሳችሁ! ማለት ነው። “ግፋታ”የወላይታ የዘመን መለወጫ ማለት ነው፤ “ዮዮ” ማለት ደግሞ ለዚህ አዲስ ዓመት አደረሳችሁ የሚል የአማርኛ አቻ ትርጉም አለው።
ግፋታ የዘመን መለወጫ በዓል ዘንድሮ ከመስቀል ጋር ተገጣጠመ እንጂ ቋሚ ሆኖ መስከረም 17 ላይ የሚከበር በዓል አይደለም፡፡ ከግፋታ ወይም ከዘመን መለወጫ አንድ ቀን አስቀድሞ የሴቶች በዓል ይከበራል።
የጨረቃ አወጣጥን ተከትሎ ከመስከረም 14 አስከ 21 ባሉት ቀናት በዓሉ የሚውልበት ቀን
ወይም ግፋታ በሀገር ሽማግሌዎች ይወሰናል።
በዚህም መሠረት ከመስከረም 14 እስከ 17 ካሉት ቀናት በአንዱ ይከበራል ማለት ነው። የዘንድሮው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ግፋታ” በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
የአማራ ክልል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክም በበዓሉ እየታደመ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን -ከወላይታ ሶዶ