
መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከሀገር እና ከሕዝብ የተሰጣቸውን አደራ በአግባቡ በመወጣት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር፣ ሕዝቦቿን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል እና በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ ዛሬም እንደ ትናንቱ በከፍተኛ የአልደፈር ባይነት ወኔ በተጠንቀቅ ሀገራቸውን እየጠበቁ ነው።
ሱዳን የመሸገው ወንጀለኛ ቡድን በልጉዲ በኩል ሀገሪቱን ለመረበሽ ያደረገው ሙከራ መክሸፉን በልጉዲ ግንባር የተሰለፉ የጦር መሪዎች እና የሠራዊት አባላት ገልጸዋል።
የውስጥም ይሁን የውጪ ጠላት ከየትኛውም አቅጣጫ ሊሰነዝር የሚችለውን ጥቃት በብቃት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት እንደሚያስከብሩ በልጉዲ ግንባር የተሰለፉ የጦር መሪዎች እና የሠራዊት አባላት አስታውቀዋል።
ሱዳን የመሸገው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን በልጉዲ በኩል ሀገሪቱን ለመረበሽ ያደረገው ሙከራ መክሸፉን የጦር መሪዎችና የሠራዊት አባላት ተናግዋል።

የኢትዮጵያን ግዛት ከወረረው የሱዳን ሠራዊት በተጨማሪም የማይካድራውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመው ወደ ሱዳን የፈረጠጡ የአሸባሪው ትህነግ ታጣቂዎች በቀጣናው መሽገው ይገኛሉ።
የመረጃ ሰዎችን በልጉዲ መስመር አስርጎ በማስገባት ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር ለማድረግም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉ ታውቋል። ነገር ግን ሠራዊቱ የፈጠረውን ጠንካራ አደረጃጀት እና የግንኙነት መረብ ተጠቅሞ ሠርጎ ለመግባት በሞከሩት ላይ የማያዳግም ርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠላት ዕድሉን ካገኘ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም። በአማራ እና አፋር ክልሎች በንጹሐን ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ግፍና በደልም የዚህ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህንን ለመካስ ብቸኛው መንገድ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ነው ብለዋል። የመጨረሻ ግባችን የማያዳግም ርምጃ ወስዶ አሸባሪውን ቡድን እስከወዲያኛው ማጥፋት ነው ያሉት የሠራዊት አባላቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ምንም አይነት ክፍተት እንዳይኖር በንቃት እየተሠራ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።

ጠላት ዳግም ማንሰራራት በማይችልበት ደረጃ ለማጥፋት በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንዳሉም ተናግረዋል።
“አሁን አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ኀይል ካላጠፋን ቀጣዩ ትውልድ ረፍት ሊኖረው አይችልም” በማለትም ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ቀን ከሌሊት በንቃት እየሠሩ እንደሆነ አመላክተዋል።
የሕዝብ ሮሮ፣ እንባ እና ደም እንዲሁም በሠራዊቱ እና በሀገር ላይ የተፈጸመው ክህደት በከንቱ እንዳይቀር አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ዳግም በማያንሰራራበት ደረጃ ለማጥፋት መሰለፋቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ከፋኖ እና ሚሊሻ ጋር ግዳጅን በጋራ እየተወጡ ነው። ሕዝቡ በማንኛውም ሁኔታ አብሮን ስላለ በርግጠኝነት በቅርቡ ጠላትን አጥፍተን ኢትዮጵያ በሰላም እንድታገኝ እናደርጋለን ብለዋል። ይህም ጊዜ አይወስድብንም ነው ያሉት።
የሀገሪቱ ሕዝብ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኀይል ሀገሪቱን ለመበታተን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ተገንዝቧል። በዚህም ልጆቹ መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ መርቆ ከመሸኘት ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው የሚገኘው። የሕዝቡ ድጋፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ የሞራል ስንቅ እንደሆነ የሠራዊት አባላቱ አንስተዋል። ሕዝብን ደጀን በማድረግ ጠላትን አድኖ ለማውጣት ሙሉ ዝግጅት መደረጉን በልጉዲ ግንባር የተሰለፉ የሠራዊት አባላትና የጦር አዛዦች ተናግረዋል።

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በመራው ሥርዓት እንደ ተቋም የሀገሪቱ የጀግንነት ልዩ ምልክት የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት የማዳከም ሥራ ተሠርቷል፣ በመከላከያ ተቋሙ ውስጥ የነበረውን የስልጣን የበላይነት ተጠቅሞ ዘረኛ አስተሳሰብ እንዲጎለብት አድርጓል፣ የነበረውን ብልሹ አሠራር የተቃወሙ የሠራዊቱ አባላትም ተቋሙን እንዲለቁ ተገድደዋል። በተጠና መልኩ በሠራዊት አባላት ላይ ብዙ በደል ሲደርስ እንደነበርም አሚኮ በልጉዲ ምሽግ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የጦር መሪዎች እና የሠራዊቱ አባላት ተናግረዋል። ይህ አሸባሪ ቡድን በሕዝብ እምቢተኝነት ከስልጣን ከተወገደ በኋላም ሀገር ለማፍረስና ሕዝቡን ዳግም ወደ ባርነት ለመክተት በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ዘግናኝ ጥቃት መፈጸሙ የሚታወስ ነው።
የሠራዊቱ አባላትም ክህደት የፈጸመውን አሸባሪ ቡድን በከፍተኛ የጀግንነት ወኔ በመመከት የማያዳግም ርምጃ ወስደዋል፣ አሁንም እየወሰዱ ይገኛሉ፤ ርምጃቸውን አጠናክረው እስከመጨረሻ እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከልጉዲ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ