በአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ከግብርና ሥራቸው የተስተጓጎሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም እንደሚሠራ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) አስታወቀ፡፡

110
ባሕር ዳር: መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ልዑክ በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ችግር ላይ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጋር መክሯል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ጎንደር እና ሌሎች አካባቢዎች አሸባሪው ትህነግ በፈፀመው ወረራ በርካታ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ለልዑኩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
እንደ ርእስ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገለጻ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለዜጎች የሚያስፈልገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ወደ አማራ ክልል መምጣቱን አድንቀው ወደ ተግባር እንዲገባም ጠይቀዋል፡፡
እንደ ርእሰ መሥተዳድሩ ማብራሪያ ሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በባለፈው ዓመት የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፤ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ጉዳቱን ታሳቢ በማድረግ የሚችለውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ ሌሎች የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችም የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ተወካይ ፋጡማ ሰይድ ድርጅታቸው በአማራ ክልል ለረጅም ዓመታት አጋር በመሆን በእርሻ ሥራዎች፣ በእንስሳትና በዓሳ ሃብት እርባታ እንዲሁም በአግሮ ኢኮሎጂ ዘርፎች እየሠራ የቆየ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ የተፈጠረው የሰላም እጦት እና መፈናቀል ያሳስበናል ነው ያሉት፡፡
ልዑኩ በክልሉ በሽብርተኛው ትህነግ ቡድን ወረራ ምክንያት ከግብርና ሥራቸው የተስተጓጎሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ምን ልበል፤ ይሄው እኔን የቀን ጨለማ ውጦኛል፤ በደላችንን የኢትዮጵያ እና የዓለም ሕዝብ ይወቅልን❞ በተሁለደሬ ወረዳ አሸባሪው ትህነግ አራት ቤተሰቦቹን የገደለበት ወጣት
Next articleትምህርት ሚኒስቴር ለአማራ ክልል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።