
ደሴ: መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪዉ የትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች (ቀበሌ 015፣ 017 እና 027) ወረራ በፈጸመበት ወቅት በርካታ ንጹሐንን ገድሏል፤ የቻለውን ንብረት ዘርፏል ያልቻለዉን ደግሞ አውድሟል ይላሉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች።
በአሸባሪው ትህነግ በግፍ ከተገደሉት ንጹሐን ዜጎች መካከል በወረዳው ❝ቀበሌ 017❞ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ተመልክተናል።
በዚህ ቀበሌ አሸባሪው ቡድኑ በተኮሰው ከባድ መሳሪያ በአንድ ቤት ውስጥ አራት የቤተሰብ አባላት ተገድለዋል። ሁለት ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል። ሰኢድ ዓሊ ይባላል። አሸባሪዉ የትህነግ ወራሪ ቡድን እናትና አባቱን ጨምሮ አራት የቤተሰብ አባላቱን በግፍ ገድሎበታል። በወቅቱ ከቤተሰቡ ጋር እንዳልነበር የገለጸው ሰኢድ እንባ እየተናነቀው ❝ምን ልበል፤ ይሄው እኔን የቀን ጨለማ ውጦኛል፤ በደላችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወቅልን። ዓለም ይወቅልን❞ ብሏል።
የቤተሰቡ ኑሮ በአባታቸው ላይ የተመሠረተ እንደነበርም ሰኢድ ገልጿል። ❝እነዚህን አረመኔዎች በአንድነት እናጥፋቸው❞ ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
አቶ አሕመድ ሁሴን አራቱን ሟች የአንድ ቤተሰብ አባላት የቀበሩ ጎረቤት ናቸው፤ ❝ቤት እንደገባሁ ብጮህ ሰሚ አጣሁ፤ ምሳ ለመብላት ወጥ እየተሠራ እያለ ነበር የፈጇቸዉ፤ አገዳደላቸዉ ምኑ ይነገራል❞ ሲሉ ሐዘን በተሞላበት ስሜት የሽብር ቡድኑን ጭካኔ አስረድተዋል። ጎረቤታቸው ሟች አቶ ዓሊ ሙሐመድን ሲገልጹ ❝ከግብርና በቀር ምንም የማያውቅ፣ ሰውን ቀና ብሎ የማያይ ነበር❞ ብለዋል።
አሸባሪዉ የትሕነግ ወራሪ ቡድን ያልፈጸመዉ የግፍ አይነት እንደሌለ የገለጹት አቶ አሕመድ ጨውና በርበሬ ሳይቀር ዘርፈዉ መውሰዳቸዉን ተናግረዋል። ❝ምኑ ተነግሮ ያልቃል፤ ከመስታወት ያነሰ ነገር የለም፤ እሱንም፣ አንካሴም ሳይቀራቸዉ ወስደውታል❞ ነው ያሉት።
አቶ አሕመድ ይህን ወራሪና አሸባሪ ቡድን ማጥፋት እንደሚገባ ተናግረዉ ለዚህም አቅማቸዉ በሚፈቅደው እንደሚያግዙ ገልጸዋል።
የአሚኮ ጋዜጠኞች ቡድን በተዘዋወረባቸው በእነዚህ አካባቢዎች የፈራረሱ ቤቶች፣ በየመንገዱ ተገድለው የወዳደቁ የእንስሳት አካል ተመልክቷል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ