
መስከረም 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኩሩ ነው የራሱ ያልሆነን የማይነካ፣ ጀግና ነው ሀገሩን ለጠላት የማያስነካ፣ ጠቢብ ነው ዘመናትን በጥበብ የሚለካ፣ ተራማጅ ነው በአንድ ድል የማይረካ። በጭንቅ ቀን የሚታመን፣ በቸገረ ጊዜ የሚለመን፣ ዘመን አሻጋሪ፣ እውነት መስካሪ፣ ለፍትሕ ተከራካሪ፣ ከሀገሩ በፊት ለሞት የሚገሰግስ፣ ለወገኑ የክብር ካባ የሚያለብስ፣ ሞት አለ ብሎ የማይፈራ፣ በሰራው ጀብዱ የማይኩራራ ነው።
ለራበው ያጎርሳል፣ ለታራዘው ያለብሳል፣ ለተጨነቀ ይደርሳል፣ በጀግንነቱ አንጀት ያርሳል፣ በሰላም ቀን አጋላብጦ ያርሳል፣ ከሰፊ አውድማ ነጭና ጥቁር ያፍሳል፣ በክፉ ቀን ዓልሞ ይተኩሳል፣ በላከው ጥይት ጅማት ይበጥሳል፣ ጠላትን በአሻገር ይመልሳል፣ ከቤቱ ሲገቡ ጠጅና ጠላ በገንቦ እየቀዳ፣ ጮማውን በነጭ ጤፍ እንጀራ እያሰናዳ ብሉ ይላል። እንግዳ ከቤቱ ገብቶ፣ ከማዕዱ በልቶ የጠገበ አይመስለውም፣ ለማብላት ❝አፈር ስሆን❞ ይላል፣ እንግዳው በልቶ በቃኝ ሲል ❝ስሞት❞ እያለ ከመሶቡ እየጠቀለለ ያጎርሳል፣ በማይገመግመው እጁ እያነሳ ያደረጉታል።
ስስት ያልፈጠረበት፣ ፈሪ ያልተወለደበት፣ ጀግና የሞላበት፣ ጠላት የቀናበት፣ ወገን የኮራበት፣ በጭንቅ ቀን የሚታመንበት፣ ለአንዲት ሠንደቅ የቆመ፣ በሀገር ፍቅር የታመመ፣ ለአንድነት የተመመም ነው አማራ። አዎን አማራ ከተራራ የገዘፈ፣ ታሪኩ በወርቅ ቀለም በማያረጅ ብራና የተፃፈ፣ ስሙ በታላቅ መዝገብ ላይ ያረፈ፣ ዘመናትን በፅናት ያለፈ፣ መቅደስ የሚያንፅ፣ አለት የሚቀርፅ፣ ሲገፉት የማይጎድል፣ በደሉኝ ብሎ የማይበድል፣ የተጣመመውን የሚያደላድል ነው።
ከሰማይ በረከት እንዲወርድ በሰርክ ለፈጣሪው ጸሎት ያደርሳል፣ ምድር ጦሟን እንዳታደር ሳይሰለች ያርሳል፣ ወገን እንዳይደፈር ገትሮ ይተኩሳል፣ የሰማዩን ማት በጸሎት፣ የምድሩን ችግር በብልሃት፣ በረቀቀ ስልት፣ እምቢ ሲል በጥይት ይመልሳል። አማራ አይከዳም፣ ከወሰነ አያወላዳም። ለሚወደው ቀድሞ መሞት፣ ራሱን አሳልፎ ሌላውን ማሰንበት ያውቅበታል። ቃሉን ከሚበላ ቢሞት ይመርጣል። ታምኖ ውሎ ታምኖ ማደር፣ ታምኖ ከርሞ ታምኖ መኖር መገለጫው ነው።
አለት ከላይ ወደታች የቀረፀ፣ ቤተመንግሥት በድንቅ ጥበብ ያነፀ ጠቢብም ነው አማራ።
ለጋሹና ታጋሹ፣ ተኳሹና አራሹ አማራ ከዋሻ አውጥቶ ማዕረግ ባሳያቸው፣ መርቶ ቤተመንግሥት ባደረሳቸው፣ ፣ አምኖ ሀገር እንዲመሩ ባደረጋቸው በከሀዲዎች ተክዶ፣ ሥራው ተረስቶ፣ ውለታው ተዘንግቶ ዛሬ ላይ ችግር ገጥሞታል። አማራ ከጎሬ አውጥቶ ከዙፋን ላይ እንዳስቀመጣቸው ሁሉ ሀገሩን ሲክዷት፣ እርሱንም ሲገፉት ከዙፋን አውርዶ ጎሬ ውስጥ ከተታቸው። ታዲያ ሲያምናቸው የከዱት፣ ሲደግፋቸው የገፉት፣ ሲያከብራቸው ክብሩን የነኩት ከሃዲዎች ክንዱን አቅምሶ ሲበታትናቸው አፈር ልሰው ዛሬም ከመግፋት አላቆሙም።
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ዛሬም አማራን ወርሯል፣ ንጹሐንን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ ሀብቱን ዘርፏል፣ ንብረቱን አውድሟል፣ ዘርፏል፣ ምን ይሄ ብቻ መማሪያ የሚሆነውን ትምህርት ቤት፣ መታከሚያውን የጤና ተቋማት አውድሟል። በወራሪው ጦስ በአካባቢያቸው መድኃኒት አጥተው የሚሰቃዩ ዜጎች በርካቶች ናቸው። አዲሱ ዓመት ሲያብት መማር የሚሹ፣ ነገር ግን መማሪያቸው የፈረሰባቸውም በርካቶች ናቸው። ወራሪው ቡድን በጀግናው ሕዝብና በጀግናው የወገን ጦር እየተመታ ባለበት እየቀረ ቢሆንም ያወደማቸውን ተቋማት ለመመለስ ብዙ ሥራ ይጠይቃል።
ይህን ችግር ያዩ አዛኞች፣ የቁርጥ ቀን ወገኖች እነርሱ ሲቸገሩ እንደምን ችለን ዝም እንላለን እያሉ ነው። ወራሪው ቡድን ውድመት ያደረሰባቸው በሰሜን ወሎ የሚገኙ ተማሪዎችን እናስተምራችሁ የሚል የአብራክ ክፋይ መጥቶላቸዋል።

❝ክፉ ቀን ሲመጣ ሲበዛ መከራ
አለሁ ይላል እንጂ አይከዳም አማራ❞ አማራ በክፉ ቀን ይቀርባል፣ በችግር ዘመን አለሁ ይላልና ለወገኖቹ አለሁ ብሏል። ከወደ ጎጃም ልጆቻችሁን ስጡንና እናስተምር፣ እንከባከብ የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ከማርና ወተቱ እያጠጣን፣ ከጮማ እያስቆረጥን፣ ከነጭ ጤፍ እያቀማጠልን ልጆቻችሁን እናስተምራለን እንጂ ዝም አንልም ብለዋል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት ለሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር እባካችሁን ልጆቻችሁን ስጡን እናስተምር ብሏል።
ወረዳው በደረሰው ጉዳት እናዝናለን፣ ነገር ግን አዝነን አንቀመጥም ነው ያለው።
ለሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር በላከው ደብዳቤ ❝… የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው የነገ ተስፋ ሕጻናት ቤት አልባ፣ ምግብ የሌላቸው እና ትምህርት ተቋማቶችም በቀላሉ የማይመለሱ መሆኑን የተረዳን ስለሆነ የምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ከ57 ትምህርት ቤቶቻችን ጋር በመግባባት ተማሪዎችን ተቀብለን ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍነን ለልጆቻችን በምናደርገው እንክብካቤ ልክ ተንከባክበን አንድ ዓመት ትምህርታቸውን ማስተማር ስለፈለግን የትኛውም የክፍል ደረጃ ፈቃደኛ የሆኑ፣ በጦርነቱ ምክንያት ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ፣ የትምህርት ተቋማት የፈረሰባቸው፣ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ ለኑሮ የተቸገሩ፣ ወላጆቻቸው አሁን ግንባር ላይ ያሉ፣ ሕጻናት ተማሪዎች ለይታችሁ ብታሳውቁን ሕዝባችን እንደተለመደው ሁሉ የአንድ ዓመት ትምህርታቸውን ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን በአስተዳደር ምክር ቤታችን በወሰነው መሠረት ስንገልፅላችሁ በታላቅ አማራዊ ስሜት ነው❞ ብሏል።
አማራ ማለት ይህ ነው ችግራችሁን ላግዛችሁ፣ ሕመማችሁን ልታመምላችሁ፣ ሞታችሁን ልሙትላችሁ የሚል፣ ወገን ማለት እንደዚህ ነው እኛ እያለን እናንተ አትቸገሩም፣ እኛ በልተን እናንተ ፆም አታድሩም፣ እኛ ስቀን እናንተ አታዝኑም፣ የእኛ ልጆች ተምረው የእናንተ ልጆች አይቀሩም፣ የእኛ ልጆች ጠግበው የእናት ልጆች አይራቡም እያለ ሐዘን የሚካፈል፣ ካለው የሚያካፍል። ወዳጄ ይህ ትርጉሙ ብዙ ነው። ስጦታው ታላቅ ነው። ጥያቄው ረቂቅ ነው።
❝ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና
ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና❞ እንደተባለ ቀን እንዳያስተዛዝብ አንተም የተቻለህን አድርግ፣ ለወገኖችህ ካለህ ነገር ከፍለህ ስጥ፣ በምድርም በሰማይም ታተርፍበታለህና። መደጋገፍ ያሻግራል፣ መተሳሰብ ያፋቅራል። ወገንህን ከወደድከው፣ ክፉውን ማዬት ከጠላኸው የቻልከውን ሁሉ አድርግ። ጠላትን በመዋጋት፣ የተቸገሩትን በመርዳት በምትችለው ሁሉ ከወገንህ አጠገብ ተገኝ።
ዛሬ የሰጠኸው ትንሽ ነገር ብዙ ሰዎችን ያተርፋል፣ ዛሬ ያደረከው ቀላል የሚመስል መልካም ስጦታ ብዙ ወገኖችህ ከችግር ያሳልፋል፣ ዛሬ የምታደርገው ጥሩ ነገር የዛሬውን ክፉ ቀን ያጠፋል፣ የነገውን ፍቅር ያሰፋል። ተነስ ለደግነት የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የተራቡትን ለማብላት፣ የተጠሙትን ለማጠጣት። ዛሬ ለደግነት ከተነሳህ ነገ በሥራህ ትኮራለህ፣ ለወገንህ መመኪያ ነህ ትባላለህ። ሁሉም የተቸገሩትን ለመርዳት ይጣደፍ፣ የተጨነቀችን ነብስ ያትርፍ። ይህን ካደረክ ነገ በኩራት ትናገራለህ፣ ሳይሆን ቢቀር ግን በታሪክ ታፍራለህ። እንዳታፍር ተነስ፣ እንዳትቀደም ገስግስ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ