
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2012 ዓ/ም (አብመድ) ዛሬ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀይማኖት ተከታዮች በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁም ነው በሰልፎቹ የጠየቁት፡፡ በሰላማዊ ሰልፎቹ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮችም ተሳትፈዋል፤ በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትም አውግዘዋል፡፡
ዛሬ ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል የሽንዲ፣ የአጅባር እና የሰቆጣ ከተሞች የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ናቸው በሰልፎቹ በመገኘት ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ያላቸውን አጋርነት የገለጹት፡፡