ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደረጉ እየሠራ መሆኑን ገለጸ።

119
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ባለመቻሉ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑ እንዳሳሰበው የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እንዳሉት ሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አልተቻለም፤ እናም በተለይ በሰሜን ወሎ ዞን፣ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ዜጎች በምግብ እና መድኃኒት እጥረት ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡
ከሽብር ቡድኑ ነጻ በወጡ አካባቢዎች አጋር አካላትን በማስተባበር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሯ አሁንም ነጻ ባልወጡ አካባቢዎች ድጋፉን ማድረስ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡ እናም የበርካታ ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን በመግለጽ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ክፍተቱን እንዲሞሉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጭምር በመጣስ ንጹሐን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርሳቸው እክል እየፈጠረ መሆኑን ወይዘሮ እታገኘሁ ተናግረዋል፡፡ በምግብ፣ መድኃኒት እና መሰል የአስቸኳይ ድጋፍ እጥረት ምክንያት ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አዛውንቶች የችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ የቀይ መስቀል ማኅበር፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ዩኤን ኦቻ በነዚህ አካባቢዎች የአስቸኳይ ድጋፍ እንዲያቀርቡ የተደረገ ቢሆንም ተግባራዊነቱ በሚፈለገው ልክ እየሄደ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ በተደጋጋሚ ባወጡት መግለጫ እና የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር ይፋ እንደሚያደርጋቸው መረጃዎች የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ለዜጎች የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ እያስተጓጎለ ነው፤ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ሥራ ያደናቅፋል፤ የእርዳታ መጋዘኖችን ይዘርፋል፤ ያወድማል፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሽከርካሪዎችን ጭምር ለጦርነት ዓላማው ሲጠቀምባቸው በሚለቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች መመልከት ተችሏል፡፡ እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ የንጹሐንን ሕይዎት እንዲታደጉ ወይዘሮ እታገኘሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ እና ዩኤን ኦቻ አዲስ አበባ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራ የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ሰመራ ከተማ ገባ።
Next article❝ክፉ ቀን ሲመጣ ሲበዛ መከራ ፣ አለሁ ይላል እንጂ አይከዳም አማራ❞