
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ በባሕር ዳር ተገኝቶ በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች እና ሀገርን ለማዳን ለተሰለፈው ወገን ጦር 385 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ምክትል ከንቲባዋ ድጋፉ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳጀር ያደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ስንፈተን እና ሲከፋን ከጎናችን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል አራት ዞኖች በከፈተው መጠነ ሰፊ ወረራ ንጹሐን ለህልፈት እና በርካቶችም ተፈናቅለዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የግለሰብና የመንግሥት ንብረት ሙሉ በሙሉ ተዘርፈዋል፤ የቀሩትም ጥቅም እንዳይሰጡ ሆነው ወድመዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ከአራት ሚሊየን በላይ ወገኖች ለከፋ ችግር ተዳርገው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ❝በዚህ ወቅት ለአማራ ሕዝብ የሚደረግ ድጋፍ ትርጉሙ ትልቅ እና ለትውልድ የሚያልፍ ታሪክ ነው❞ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት የወረራው ግብ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቢሆንም የአማራ ሕዝብ ፊት ስለተገኘ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጥቃት ተሰንዝሯል ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅትም የክልሉ ወጣቶች፣ ልዩ ኀይል፣ ሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ከአሸባሪው እና ወራሪውን ቡድን ጋር እልክ አስጨራሽ ትግል እያደረጉ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

መስዋእትነት ከፍለን አሸባሪውን ቡድን ድል እንደምናደርገው እርግጥ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ኢትዮጵያን በባንዳ እና ተላላኪ ማፍረስ እንደማይቻል ለመጨረሻ ጊዜ ትምህርት ይወሰድበታል ብለዋል፡፡
የተዘረፉት ንብረቶች፣ የተጋዘው የባለሃብቶች እና የተቋማት ንብረት ትግራይን በዘረፋ መገንባት እንደፈለጉ ይናገራል፤ ነገር ግን ወደ አማራ ክልል የገባው የአሸባሪው ቡድን መውጣቱ የመግባቱን ያክል ቀላል አይሆንም ነው ያሉት፡፡
በጦርነቱ በርካቶች ከቀያቸው ተፋናቅለዋል፣ ከአራት ሚሊየን ሕዝብ በላይ አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ይሻል፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመሻገር እና ለዜጎች ሕይዎት ለመድረስ ሁሉም የሚቻለውን በማድረግ እንዲተባበር ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
10