
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ ባሕር ዳር ገብቷል። ምክትል ከንቲባ አዳነች ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች ❝ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የገጠማቸውን የሕልውና ፈተና ለመቀልበስ የአማራ ሕዝብ ከሀገሪቱ ጥምር ጦር ጋር ተቀናጅቶ ዋጋ እየከፈለ ነው❞ ብለዋል።
ይህን የኢትዮጵያን የፈተና ወቅት በድል ተሻግረን በከፍታዋ ማማ ላይ ዳግም ኢትዮጵያን እናያታለን ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የአማራ ሕዝብ እየፈጸመው ያለው ጀግንነት እና እየከፈለው ያለው ዋጋ ታሪክ እንደማይረሳው ገልጸዋል።
የእናት ጡት ነካሾች ሀገሪቱን ከውስጥም ከውጭም ረፍት ለመንሳት የሚያደርጉት የተልእኮ ጦርነት አንድነታችን እና ብሔራዊ ጥቅማችን በጋራ እንድጠብቅ እድልም ሰጥቶናል ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ክሕደት ማንነቱን አሳይቶናል ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች ጦርነት ባይመጣ መልካም ነበር፤ ነገር ግን መምጣቱ ስጋት ብቻ ሳይሆን የምንፈልገውን ተስፋም አሳይቶናል ነው ያሉት። ምርጫችን እና መፍትሔው በጋራ መቆም ነው፤ ከሀገር ወጭ ጠላቶች እስከ ሀገር ውስጥ ተላላኪዎች የተቃጣብንን ትንኮሳ እናሸንፋለን ብለዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ በከፈተው ወረራ ንጽሐን ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት፣ የሞራል ስብራት ደርሶባቸዋል እንዲሁም በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ተጋልጠዋል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ። ይህንን ጉዳት ባይተካ እንኳን የአዲስ አበባ ሕዝብ እና የከተማ አስተዳደሩ ከጎናችሁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የ385 ሚሊየን ብር ድጋፍ አበርክተናል ነው ያሉት።
ድጋፉ የሕልውና ዘመቻው እስኪጠናቀቅ፣ ተጎጆዎች እስኪቋቋሙ እና ኢትዮጽያ ወደ ከፍታ ማማዋ እስክትዘልቅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካበረከተው የ385 ሚሊየን ብር ድጋፍ ውስጥ 35 ሚሊየን ብር የሚገመተው በዓይነት የቀረበ ድጋፍ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m