
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2012 ዓ/ም (አብመድ) በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
“በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ይቁም!፤ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሊገነቡ ይገባል፤ ሀገርን ከነክብሩ፣ ዘመንን ከነአቆጣጠሩ፣ አንድነትን ከነፍቅሩ ያቆየች ቤተ ክርስቲያን ውለታዋ ይህ ሊሆን አይገባም፤ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው!” የሚሉ መልዕክቶች በሰልፎቹ ተስተጋብተዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን መንግሥት ተጠያቂ እንዲያደርግም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
ዛሬ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር በሰቆጣ ከተማ እና ወረዳ ፣ በዝቋላ ወረዳ – ፅፅቃ ከተማ፣ በድሃና ወረዳ – አምደ ወርቅ ከተማ፣ በጋዝጊብላ ወረዳ – አስከተማ፣ በሰሃላሰየምት ወረዳ – መሸሀ፣ በጻግብጂ ወረዳ – በጻታ ከተማ፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደግሞ በደምበጫ እና በቋሪት ከተሞች፣ በወምበርማ ወረዳ – ሺንዲ ከተማ ነው ዛሬ ሰላማዊ ሰልፎች የተካሄዱት፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ – አጅባር ከተማ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ – ድል ይብዛ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተካሄደም ታውቋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፎቹም የአቋም መግለጫ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና መከራ የሚያወግዙ እና ድርጊቱ እንዲስተካከል የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች በአማራ ክልል ከመስከረም 4/2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት መካሄዳቸውም ይታወሳል፡፡