ኢትዮጵያን በውጭ የሚወክሏት ሚሲዮኖች በአዲስ መልኩ ሊዋቀሩ ነው፡፡

307
አዲስ አበባ፡ መስከረም 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን በውጭ የሚወክሏት ሚሲዮኖች ጥናትን መሰረት በማድረግ በአዲስ መልኩ እንደሚዋቀሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለውጡን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም የሚያስችለውን የአሠራር ማሻሻያ እያደረገ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም ላለፉት ስድስት ወራት ሲከናወኑ የነበሩ የአሠራር ማሻሻያ ጥናቶችና ተግባራቶች አሁን ላይ ከሞላ ጎደል ተጠናቅቀው ለትግበራ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
ለዲፕሎማቶችና ለተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ማሻሻያ በተደረጉባቸው የተቋሙ አሠራሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝየ ያስችላል ብለዋል።
የአሠራር ማሻሻያዎቹ ተቋሙ የተጣለበትን ኀላፊነትና ተልዕኮዎች በብቃት ለመወጣት ታሳቢ ተደርጎና ጥናት ላይ መሰረት በማድረግ የተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። በተለይ ዋና መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የዲፕማሲ ሥራው የሚያሳልጥ ዋነኛ ማዕከል እንዲሆን ታልሞ የተካሄደ የአሠራር ማሻሻያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚሲዮኖችና ቆንጽላዎች የሚያከናውኑትን ተግባራት፣ የሚያጋጥማቸውን ፈተናና ያሏቸው እድሎችን ከግምት ያስገባ ግምገማ እንደተደረገባቸውም ተናግረዋል።
ጥናትን መሰረት በማድረግና የአጋር አካላትን ምክረ ሐሳብ ከግምት በማስገባት ሚሲዮኖቹን በአዲስ መልኩ የማዋቀር ሥራ እንደሚሠራም ነው ያረጋገጡት።ይህንንም ተከትሎ ዲፕሎማቶችን በእነዚሁ ሚሲዮኖች የመመደብ ሥራ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ሠልጣኞቹ በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ኀይሎች እየደረሰ ያለውን ጫና ከግምት ያስገባ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሥልጠናው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ለውጦች ከግምት ያስገባ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ለማጎልበት ትኩረት ያደርጋልም ነው የተባለው።
መደበኛ የዲፕሎማሲያዊ አሠራር ከዲጂታል ዲፕሎማሲ ጋር በማጣመር የሚሲዮኖች ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችሉ ጉዳዮችም ሌላኛው የሥልጠናው ትኩረት ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ ሀገራዊና ተቋማዊ የአሠራር ለውጥ ላይ ለሠልጣኞቹ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል ተብሏል። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው የሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲያቀርቡ ከዞኑ የተፈናቀሉ ወገኖች ጠየቁ።
Next articleየአማራ ክልል ባለሃብቶች በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ፡፡