
መስከረም 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና በአካባቢው ማኅበረሰብ ከደቡብ ጎንደር ዞን ጋሳይ ከተማ ጀምሮ እየተቀጠቀጠ እስከ ሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና ከተማ ደርሷል።
ቡድኑ በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ የጋሳይ፣ ክምር ድንጋይ፣ ጎብጎብ፣ ነፋስ መውጫና ሌሎችም አካባቢዎች ተጠራርጎ እስኪወጣ ድረስ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር መጠነ ሠፊ ዘረፋና ውድመት ማድረጉን የአሚኮ ጋዜጠኞች ቡድን በስፍራው ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል።
አሁንም የሽብር ቡድኑ በደረሰበት ጭፍጨፋ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የሚገኙ ደብረ ዘቢጥ፣ ኮኪት፣ አግሪት፣ ፍላቂትና ገረገራን ለመልቀቅ ተገዷል።

ቡድኑ እንደልማዱ በእነዚህ አካባቢዎችም የሚያደርሰውን ውድመት ቀጥሎበታል። የፍላቂት ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ጎበዜ በዛብህ አሸባሪው ቡድን በከተማዋ ውስጥ ባደረገው ቆይታ “የሚበላ አምጣ” በማለት ኅብረተሰቡን ሲያስቸግር እንደቆየ ተናግሯል። ቡድኑ ጉልበቱን በመጠቀም የሚበላና የሚጠጣ ሲቀማ እንደቆየ ነው ወጣቱ የተናገረው።

የገረገራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ገነት አበባው አሸባሪው ቡድን በከተማዋ ውስጥ ባደረገው ቆይታ የቤት አስቤዛዎችን ጠራርጎ በመውሰድ ኅብረተሰቡን የሚበላ እንዳሳጡት ተናግረዋል።

የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድም ገረገራ ከተማ በመገኘት ኅብረተሰቡ ከሽብር ቡድኑ ነፃ ከወጣ በኋላ የተሰማውን ደስታ ለመመልከት ችሏል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከገረገራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ