
ደባረቅ፡ መስከረም 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተመራው የባለሀብቶች ቡድን በስሜን ጎንደር ዞን ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ለሠራዊቱ ድጋፍ አድርጓል።
ሚኒስትሩ የመሩት የባለሀብቶች ቡድን ከተጎጂዎች ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ የኢፌዴሪ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን፣ የምእራብ እዝ ምክትል አዛዥ ብራጋዴር ጄኔራል ሰይድ ትኩዬ፣ የስሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን፣ ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴን ጨምሮ ባለሀብቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የዞኑ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ተጎጂዎች ወራሪው ቡድን ንፁሃንን ገደልሏል፣ ሀብት ዘርፏል፣ የእለት ጉርስና የአመት ልብስ ነስቶናል ነው ያሉት። የተዘራው አዝመራ ጥቅም እንዳይሰጥ አድርገውት ሸሽተዋልም ብለዋል። ሰው መጠጊያ እስኪያጣ ድረስ መዝረፋቸውንም ተናግረዋል።
ዳግማዊ ማይካድራ ተፈፅሞብናልም ነው ያሉት። ቤተክርስቲያንን ምሽግ አድርገው መዋጋታቸውን እና የእምነት ተቋማትን መዝረፋቸውን ገልፀዋል። ቅሳውስትንና ሼሆችንም ገድለዋል፣ ሕዝብና ሃይማኖትን ማጥፋት የወራሪው ቡድን ቀዳሚ ዓላማ መሆኑንም ገልፀዋል።
ፋኖና ሚሊሻ ልጆቻችሁን አምጡ እየተባልን ተንገላተናልም ነው ያሉት። እናቶችን በግፍ መድፈራቸውንም ገልፀዋል። በጉዳቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የዘረፈውና የገደለው ቡድን በዚያው በመቅረቱ ደስተኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ተጎጂዎቹ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን ጀግና ሕዝብ አለን ነው ያሉት። ጦርነቱ አሁንም ገና መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው ከ75በ ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በዞኑ መኖራቸውን ገልፀዋል። ወጣቱ አሁን ካለበት በላይ ካልተደራጄና መከላከያ ሠራዊትን ካልተቀላቀለ ድሉ ዘላቂ አይሆንምም ብለዋል። ስሜን ጎንደር የገባ ጠላት መመለስ የለበትምም ብለዋል። ስለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ የመጣነው ችግራችሁን ለመካፈልና ከጀግነታችሁ ለመቋደስ ነው ብለዋል። ራስ ወዳድ የሆነው ቡድን ከሌለው ጋር አብሬ እኖራለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም፣ አማራን አጥፍቼ እኖራለሁ የሚል ነውም ብለዋል። አጥፍቼ እኖራለሁ ለሚል ቡድን ተደራጅተን ከመዋጋት በስተቀር ሌላ የሚያድነን የለም ነው ያሉት። ክንዳችን አጠንክረን መታገል አለብን ያሉት ባለሀብቱ ሀገርና ቤተሰብን የሚከፋፍል ቡድን እስኪጠፋ ድረስ ተባብረን መታገል አለብን ነው ያሉት። ጦርነቱ ፍትሓዊ መሆኑንም ገልፀዋል።
የባለሀብቱ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ጠላትን አፈር ካላስገባን ሰላም አናገኝምም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እያለ ጦማችሁን አያሳድራችሁምም ነው ያሉት። የአባቶቻችሁን ታሪክ ስለ ደገማችሁት ልትኮሩ ይገባልም ነው ያሉት። አሁን ላይ ጨክኖ ጠላትን ማጥፋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

800 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቃዮች እና አንድ መኪና ዘይት ለሠራዊቱ ማቅረባቸውንም ገልፀዋል። የቆርቆሮ ጥያቄ ተጠንቶ ይቀረብልን እናቀርባለን፣ አብረን ነው ያለን ጥለናችሁ አንበላምም ብለዋል።
የምእራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሰይድ ትኩዬ በደባርቅና ዳባት ቆርጦ ከቅማንት ፅንፈኛ ቡድንና ሱዳን ከመሸገው የአሸባሪው ስደተኛ ቡድን ጋር በመገናኘት የሑመራን ኮሊደር ሊከፍት የነበረው ቡድን ሕልሙ ቅዠት ሆኖ መደምሱን አስታውሰዋል። ለተገኘው ድል የአካባቢው ማኅበረሰብ በተወለድንበት ቦታ እኛ እንሞታለን እንጂ እናንተ አትሞቱም በማለት ያሳዬው ጀግንነት የሚገረም እንደነበርም ተናግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ከውጊያ ባለፈ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ነው ያሉት። ድሉ የማኅበረሰቡ ድል ነውም ብለዋል። በማኅበረሰቡም ኮርተናል ብለዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታው ፈንታ ደጀን አማራን ካለጠፋሁ ብሎ የተነሳውን ወራሪ ቡድን በመደምሰሳችሁ ኩራት ይገባችኋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት እንዳሰበው እንዳይሆን አድርጎ እንደቀጣውም ገልፀዋል። አማራ ጠል የሆነው ቡድን የአማራን ሀብት አውድሟል፣ የሃይማኖት ተቋማትንም ዘርፏል ነው ያሉት። ወራሪውን ቡድን እስከመጨረሻው ድረስ ማስወገድ የአማራና የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ዓላማ መሆን አለበትም ብለዋል። ከዚህ በኋላ ገፍተን አንተውም ተከታትለን መቅበር ይገባል ነው ያሉት። ሕዝቡ በመደራጀት ጠላትን መቅበር እና ለሠራዊቱ ደጀን መሆኑን መቀጠል አለበትም ብለዋል። ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል መታገል እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ሚኒስተሩ መላኩ አለበል ለተገኘው ድል አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነዋል። መሬቱ በመልካም ጊዜ ያበላውን በክፉ ጊዜ በልቷል ነው ያሉት። ወራሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሕዝቦቿን ለማንበርከክ ጭካኔ የተመላበትን ሲፈጸም ሕዝቡ ትክክለኛ ደጀንነቱን ማሳየቱን ተናግረዋል። ሕዘቡ ለጦርነቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጠላት ከውጭ ጠላት በበለጠ መልኩ ግፍ መፈፀሙንም ተናግረዋል። ሀገር በመስዋእትነት እንደምትጠብቅ ያነሱት ሚኒስትሩ የኃይል ሚዛን በማይመጣጠንበት ዘመን ጠላትን የመለሰ ሕዝብ የሽፍታን ቡድን የማያሸንፍበት ምክንያት የለምም ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለ ፅኑ መሠረት ሆና እንጂ ሀገር ለማፍረስ ከብዙ ኃይሎች ጋር መሥራቱን አስታውሰዋል።
ካለፈው በመማር፣ ጨክኖ በመገኘት፣ በመደራጀት፣ በትንንሽ ድሎች ባለመዘናጋት፣ በሚደርሱት በደሎች ባለመሸማቀቅ ጠላትን እስከመጨረሻው ማጥፋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም ይጠበቅብናልም ብለዋል። በማኅበረሰቡ ላይ የሥነልቦና ችግር እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶችና የሥነልቦና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። መንግሥትም የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይሠራል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጋር ያለውን ቅንጅት ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ባለሀብቶቹ እስካሁን ድረስ በማይጠብሪ ግንባር ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል። ባለሀብቱ መንግሥት ማቅረብ የማይችለውን እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል። ዛሬ በማይጠብሪ፣ 800 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቃዮች፣ መቶ ሰንጋዎች፣ አንድ መኪና ዘይት ለሠራዊቱ ድጋፍ አድርገዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ–ከማይጠብሪ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ