የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለአፋር ክልል የ25 ሚሊዮን ብርና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

192
ሰመራ፡ መስከረም 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ድጋፉን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ርስቱ ይርዳው ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ሰመራ በመገኘት ለአፋር ክልል ርእስ መሥተዳድር ሐጂ አወል አርባ አስረክበዋል። የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ እየተፋለሙ ለሚገኙ ኀይሎችና ለተፈናቃይ ወገኖች የሚውል ነው ተብሏል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ርስቱ ይርዳው የአፋር ሕዝብ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ ኢትዮጵያን የሚጠበቃት ከለላ ነውም ነው ያሉት።
“በአፋሮች ላይ በአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል፣ በዚህም የሕፃናትና የአቅመ ደካሞች ህይወት በጅምላ ተቀጥፏል፣ ሀብትና ንብረቶቻቸው ወድመዋል፣ ተፈናቅለዋል። አቃፊነትን በተግባር ያሳየው ሕዝብ ይህ አይገባውም ነበር። እርግጥ የአሸባሪ ቡድኑ ጠላት የአፋርና የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን ነው። ክልሉ ሁልጊዜም ከአፋር ሕዝብ ጎን ይቆማል” ብለዋል አቶ ርስቱ።
የአፋር ጀግኖች ላሳዩን ታሪካዊ ገድል እናመሰግናቸዋለንም፤ እኛ አስፈላጊውን መስዋእትነት ሁሉ ከፍለን የሀገራችንን ክብር ማስጠበቅ ይኖርብናል ነው ያሉት።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጸጥታ መዋቅሩ የሚያደርገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በሚደረገው ድጋፍም ቤተሰብ ሆነን እንቆማለን ብለዋል። ክልሉ የ25 ሚሊዮን ብርና የ800 ኩንታል ስንዴና የ8 ሺህ ሊትር ዘይት ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ርእስ መሥተዳድር ሐጂ አወል አርባ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ በመሥራት በአጭር ጊዜ ደግሞ በአፋር በኩል የወጪና ገቢ ንግድ መስመሩን በመዝጋት ኢትዮጵያን ለድርድር የማቅረብ ህልም ነበረው ብለዋል። አሸባሪ ቡድኑ ለፍተው ለሚያድሩ የአፋርና የአማራ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ህይወትም ንብረትም እንደማይሳሳ በተግባር አሳይቶናል ነው ያሉት።
ጋሊኮማ ላይ መሸሽ የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ጨፍጭፏል፤ በተለያዩ አካባቢዎችም ሙከራዎችን አድርጓል። አሁን ግን ህልሙን ማሳካት እንደማይችል አሳይተነዋልም ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ያለው በአፋርና አማራ ግንባር ብቻ ሳይሆን በፈጠራቸው ሴሎች በሁሉም አካባቢዎች ነው። አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኀይል የሚላላኩትን ፈጥሯል፤ ራሱ ደግሞ ለፀረ ኢትዮጵያ ኀይሎች ይላላካል ብለዋል። እኛ ጠላታችንን በአጭር ጊዜ መጨረስ አለብን። የአማራን አርሶአደር እየበደለ ከኛ ክልል ለቆ ወጥቷል ብለን የምንቀመጥበት ምክንያት የለም ነው ያሉት ። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበተከዜ ግንባር 21 ጊዜ የማጥቃት ሙከራ ያደረገው አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በምኒልክ ብርጌድ በተደጋጋሚ አሳፋሪ ሽንፈት ደርሶበታል።
Next articleበንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተመራው የባለሀብቶች ቡድን በማይጠብሪ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦርና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።