
ባሕር ዳር፡ መስከረም 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ወረራ ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጅ ድረስ ያሉ የትምህርት ተቋማት የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ አሸባሪው ትህነግ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የነበሩ የመማር ማስተማሪያ ግብዓቶችን ዘርፏል፤ ማንቀሳቀስ ያልቻለውን ደግሞ ጥቅም በማይሰጥ መልኩ አውድሟል፡፡
ንጹሃንን የጥቃቱ ዒላማ፤ መሰረተ ልማቶችን ማውደም ደግሞ ግቡ አድርጎ ወረራ የፈጸመው አሸባሪው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ላይ አስነዋሪ ጉዳት አድርሷል፡፡ በወረራው በአማራ ክልል ብቻ በተለያዩ ቦታዎች ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ፈጽሟል፡፡ አሸባሪው ቡድን ባደረሰው ጉዳት ከአራት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፤ 2 ሺህ 511 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጥቃት ደርሶባቸዋል ያሉት በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜ መረጃዎቹ ሲጣሩ የጉዳቱ መጠን ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ያስተናግዱ የነበሩ እንደሆነም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ያላቸው ሃብት እና ንብረት ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል፤ አሸባሪ ቡድኑ ማንቀሳቀስ ያልቻለውን ደግሞ ጥቅም በማይሰጡበት መንገድ አውድሟቸዋል ብለዋል፡፡ ከፊል ጉዳት በሚል የተጠቀሱትም ሃብት እና ንብረታቸው ተዘርፎ ሕንፃዎቹ ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸውን የትምህርት ተቋማት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ጌታቸው ነፃ በወጡ አካባቢዎች ያለውን የጉዳት መጠን የሚያጠና ቡድን ወደ አካባቢዎቹ እንደተላከም ጠቁመዋል፡፡ በተቋማቱ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በመለየት የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በቅርቡ ለመጀመር እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ በመሆኑ የመንግሥትን፣ የተራድኦ ድርጅቶችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን እና የክልሉ ነዋሪዎችን ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ከተቋማት እና በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ድጋፍ ይሻሉም ተብሏል፡፡ የክልሉ መንግሥት እያሰራቸው ያሉ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች በወረራው ለተጎዱ አካባቢዎች በቅድሚያ ይሰራጫሉም ተብሏል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት እና የጽሕፈት ቤት ኅላፊው ትምህርት ቤቶቹን መልሶ በመገንባት፣ የተማሪዎችን እና የማኅበረሰቡን ሥነ-ልቦና መልሶ በመጠገን እና ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት መዋቅሩም በየደረጃው የምክክር መድረክ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስር ያሉት የሰቆጣ እና የወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጆችም በአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ጉዳት እና ዘረፋ እንደደረሰባቸው ከትምህርት ቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ እነዚህን ኮሌጆች መልሶ በመገንባት እና ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ የሚያስችል ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ