
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2012 ዓ/ም (አብመድ) በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ – አጅባር ከተማ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖት ተከታይ ምዕመናን እና የሀይማኖት አባቶች ናቸው ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ የሚገኙት፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚጠይቁ መልዕክቶች በሰልፉ እየተስተጋቡ ነው፡፡
በሰልፉ እየተላለፉ ከሚገኙት መልዕክቶች መካከል “ሀገርን ከነድንበሩ፣ ነፃነትን ከነክብሩ፣ ፊደልን ከነቁጥሩ፣ አንድነትን ከነጀግንነቱ ለሀገር ያስረከበች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቃጠል ፈጽሞ አይገባትም!፤ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል የኢትዮጵያን የታሪክ አሻራ ማጥፋት ነው፤ የፖለቲካ ነጋዴዎች እጃችሁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሱ!” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ተሳትፈዋል፤ በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ድርጊትም አውግዘዋል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ሳይንት ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት