“የሶማሌ ሕዝብ በዚህ ትግል ብቻ ሳይሆን ከሶስት ሀገራት ጋር በሺህ ኪሎሜትሮች የሚያዋስኑ የሀገሪቱን ድንበር በመጠበቅ የሀገርን ሉዓላዊነት እያስከበረ ነው” የሶማሌ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጅነር መሀመድ ሻሌ

255

ደሴ፡ መስከረም 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሰለፍ እየተፋለሙ ይገኛሉ። የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም በወሎ ግንባር አሸባሪውን ቡድን በመፋለም ላይ የሚገኘውን የወገን ጦር በትናንትናው ዕለት ጎብኝተዋል።

በግንባሩ ከተገኙት መካከል ደግሞ የሶማሌ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጅነር መሀመድ ሻሌ አንዱ ናቸው። ኢንጅነር መሀመድ እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ ባለፉት 27 ዓመታት ሲከተል በነበረው አግላይ ርዕዮተ ዓለም በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል ፈጽሟል።

አሸባሪው ቡድን የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት የሀገርን ክብር አዋርዷል። በዚህ ወቅትም በሀገሪቱ ላይ የፈጸመውን ወረራ ለመከላከል በሚደረገው ትግል የክልሉ ሕዝብ እና ልዩ ኃይል በጀግንነት እየተፋለመ ይገኛል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ህዝብ እና ልዩ ኃይል በዚህ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን በሺህ ኪሎ ሜትሮች ከሶስት ሀገራት ጋር አዋሳኝ የሆኑ ቦታዎችን በመጠበቅ የሀገርን ሉዓላዊነት እያስከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም በሰላም ማስከበር እና በተለያዩ የሀገር ግዳጆች ላይ በመሳተፍ የሀገሪቱን ስም ማስጠራቱን አንስተዋል። የክልሉ ሕዝብም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ልዩነት ውበት መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር መሀመድ፣ በእኩልነት እና በመቻቻል ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል።

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሠማ እንዳሉት ደግሞ አሸባሪው ትህነግ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ኢሞራላዊ እና ኢሰብዓዊ እንደመሆኑ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ባለፉት 30 ዓመታት ገድሏል፤ አዋርዷል፤ የሀገሪቱን ንብረትም ዘርፏል። በዚህ ግፍና በደል በመንገሽገሽ በሕዝብ ማዕበል ከመንበረ ስልጣኑ የተባረረው አሸባሪ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸም ጀምሮ ሀገር የማፍረስ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንደሚወርድ መዛቱም የቆየ ድብቅ ዓላማውን በግልጽ አሳይቷል ነው ያሉት አቶ ፈቃዱ። ኢትዮጵያውያን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት እና በደምና አጥንት የተሳሰሩ ሕዝቦች የሚኖሩባትን ሀገር ማንም በፈለገ ጊዜ ተነስቶ የሚያፈራርሳት አለመሆኗን ገልጸዋል።

ይህንን የአሸባሪውን ሀገርን የማፍረስ ቅዠት ለማክሸፍ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት እየተፋለመ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን አፍራሽ ቡድን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል አንድነቱን አሁን ካሳየው በላይ በማጠናከር ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገር ለመጭው ትውልድ እስከ ክብሯ የማስረከብ ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article❝የደቡብ ክልል ሕዝብ ያደረገውን ድጋፍ የአማራ ሕዝብ ምንጊዜም አይረሳውም❞ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next articleጠላት መልሶ እንዳይቋቋም ካደረጉት ምት መካከል የዛሪማ ምት አንዱ መሆኑን የግንባሩ የክፍለ ጦር አዛዥ ተናገሩ።