የመስቀል በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ የጎብኚዎችን ቁጥር እንዳሳደገው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

513

ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2012 ዓ/ም (አብመድ) የመስቀል በዓል ኃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ባህሉን ሳይለቅ ለዓለም ሁሉ እንዲተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ካለው ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ፋይዳ አንጻር የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ የመስቀል በዓል ሲቃረብ የዓለም ዐይኖች ወደ ኢትዮጵያ ያነጣጥራሉ፡፡ የአደባባይ ትዕይንቱ፣ የምዕመናኑ አለባበስ፣ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚፈጥሩት ድንቅ ገጽታ አስደማሚ ነውና፡፡ እናም እንኳንስ በአካል የታደሙት በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተመለከቱት ይደመማሉ፤ አከባበሩን በአካል ለመመልከትም ይጓጓሉ፡፡ የውጭ ሀገራት ዜጎች በአከባበሩ ይደመማሉ፤ በበዓላቱ የመታደም ዕድሉን ያገኙት ሚመሰክሩትም ይህንኑ ነው፡፡ እናም የቻሉት በአካል ይታደማሉ፤ ያልቻሉት ደግሞ መረጃውን በሚያኙበት የመገናኛ ዘዴ ሁሉ ይከታተሉ፤ የበዓሉ ትዕይንት ልዩ ነውና፡፡

ይህን አስደናቂ በዓል የተመለከተው የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) መስቀልን “የዓለም ቅርስ ነው” ሲል መዝግቦታል፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም ሕዝብ አዲስ ብስራት ነበር፡፡ ለመሆኑ የመስቀል በዓል ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ምን አስተዋጽዖ አሳድሯል ? በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ነጋሽ በተለይም ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት የመስቀል በዓል ለአብሮነት እና ለቱሪዝም ፍሰቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በዓሉ የአደባባይ በዓል በመሆኑ ከኢኮኖሚው በዘለለ ለማኅበራዊ ትስስሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚፈጥርም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የመስቀል በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ በዓሉን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣም ነው የተናገሩት፡፡ መስቀል በኢትዮጵያ ከሚከበሩና የቱሪስትን ቀልብ ከሚስቡ በዓላት መካከል ከግንባር ቀደሞቹ እንደሚጠቀስ የተናገሩት አቶ ታሪኩ በዓሉ ሀገሪቱ ባህል፣ ታሪክና አጠቃላይ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትውፊቶቿን የምታስተዋውቅበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመስቀል በዓል ኃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ባህሉን ሳይለቅ ለዓለም ሁሉ እንዲዳረስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራበት መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡ የመስቀል በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ በዓሉን የሚያክበሩ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ነው፡፡ የመስቀል እና የግሸን ደብረ ክርቤ በዓልን ለማክበር ወደ ግሸን ማርያም የሚሄዱ ዜጎች እና ጎብኝዎች ቁጥር 3 ሚሊዮን እንደሚደርስም ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው እና ከማኅበራዊ ድረ ገጽ

Previous articleኢትዮጵያ በለተሰንበት ግደይ አማካኝነት የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አገኘች፡፡
Next articleየአጅባር ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች በቤተ ክርስቲኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው፡፡