የኢትዮጵያ የ2013 ክራሞት

111

ባሕር ዳር፡ መስከረም 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓሏን ከቀሪው ዓለም በተለየ በ13 ወራት አንጓ አስልታ እና ቀምራ ታሳልፋለች፡፡ ክፉና ደጉን፣ ጨለማና ብርሃኑን፣ ዝናብ እና ጭቃውን በምስጋና ሸኝታ አዲሱን በተስፋ እና በጉጉት ትቀበላለች፡፡ በአዲስ ዓመት ከሀገር እስከ ግለሰብ ለአዲስ ስኬት እና ግብ እቅድ ያስቀምጣሉ፡፡ ትጋት፣ ጽናት እና ብርታት በአዲስ ዓመት እንደ አዲስ ጉልበት ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ 2013 ዓመተ ምህረትን ስትቀበል ያለፉ ዘመናት ሶንኮፎቿን ነቅላ በአዲስ መንፈስ አዲስ ጉዞ ለመጀመር ነበር፡፡ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ያለፉ ቁርሾዎቻቸው ታክመው፣ ልዩነቶቻቸው ጠበው እና ክፍተቶቻቸው ተሞልተው ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና ኢትዮጵያን የማየት ሕልም ነበራቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የፓለቲካ ድባቡ የበላይነቱን በወሰደት 2013 ዓ.ም ከብዙ በጥቂቱ እንኳር ክስተቶቹ የሚከተሉት ነበሩ…

ከነገረ ቀደም ያለፉት ሦስት ዓመታት የሀገራዊ ለውጡ ጉዞ አልጥም እና አልዋጥ ያለው የቀድሞው ሀገረ መንግሥት አድራጊ ፈጣሪ ሽብርተኛው ትህነግ በሀገሪቱ እንደራሴዎች አሸባሪ ተብሎ ከመፈረጁ ቀድሞ በ2013 ዓ.ም ዋዜማ ጳጉሜን 4/2012 ዓ.ም ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ ክልላዊ ምርጫ አካሂዶ አዲሱን ዓመት በላቀ ትንኮሳ ጀመረው፡፡

በሽብርተኛው ትህነግ እብሪተኛ አቋም ገደብ የጣሱ እና ቀይ መስመር ያለፉ ድርጊቶች በ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት መጀመሪያ ወቅት መታየት ጀመሩ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በሸፍጥ ፖለቲካ ታውኳል ያለው የለውጥ አመራር ሌላ ምጣኔ ሃብታዊ አንድምታ ያለው የመገበያያ ገንዘብ ኖት ቅያሬን ለዜጎቹ ጆሮ አደረሰ፡፡ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ለቅያሬው ምክንያት ተደርገውም ቀረቡ፡፡

በሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ለተወሰኑ ወራት የሀገሪቱን ሕዝብ ጆሮ እና ቀልብ ስቦም ቆይቶ ነበር፡፡ በተለይም በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በሱማሌ እና ሌሎች ክልሎች የተከሰተው መጠነ ሰፊ የአንበጣ መንጋ የሀገሪቱን የምርት መጠን በእጅጉ ጎድቶት አልፏል፡፡

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገሪቱ 70 በመቶ የጦር ሎጀስቲክስ እና የሰው ኃይልን እንደያዘ የሚገመተው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ አስነዋሪ ጥቃት በሽብርተኛው ትህነግ ተፈጸመ፡፡ እናም መንግሥት ሕግ ወደ ማስከበር ዘመቻ ገባ፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከፌዴራል መንግሥቱም በላይ ጠላቴ ነው ያለውን የአማራ ክልል ለመውጋት ያደረገው ተከታታይ ሙከራ በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይል እና በአማራ ሚሊሻ ተዓምራዊ ጀብዱ ግስጋሴው እንዲገታ እና በዳንሻ በኩል የተከበበው 5ኛ ሜካናይዝድ ጦር ነፃ እንዲወጣ አደረጉት፡፡ የመንግሥት ጦር በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩ በፊት ሽብርተኛው ትህነግ በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና አስመራ ሮኬቶችን ወራወረ፡፡ ሠራዊቱ ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ በመሃል ሀገር አንፃራዊ ሰላም ቢፈጠርም በትግራይ የነበረው ውጥረት ግን ዘርፈ ብዙ ነበር፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ጊዜያት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር በዘረጋው መጠነ ሰፊ ሕገ ወጥ ትስስር ምክንያት የውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ከማዕቀብ እስከ ጫና፤ ከሸፍጥ እስከ ነውጥ የቻሉትን ሁሉ በሀገሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል፡፡ በዚህም አሜሪካ እና ግብረ አበሮቿ በሀገሪቱ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ላይ የቪዛ ክልከላ እስከ መጣል ደርሰዋል፡፡

ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምራ ከጦርነት ብዙም ያልራቀችው ኢትዮጵያ የሀገሪቱ እንደራሴዎች ለግጭት እና ሽብር ምንጮች ናቸው ያሏቸውን ኦነግ ሸኔን እና ትህነግን በሽብርተኝነት ፈረጁ፡፡ በመቀጠልም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ደረጃ የጤና ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያክል ያራዘመችውን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ አካሄደች፡፡ በሀገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ከምርጫ ሂደቱ ጋር ተዳምሮ ለደም አፋሳሽ ግጭት ይዳርጋል የሚሉ ቢበዙም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ያለምንም የፀጥታ ችግር ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ከሚደርስባት የጫና መንስኤዎች መካከል አንዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡ በግድቡ ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ጫናው አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ሲል ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው 2013 ዓ.ም የክረምት ወራት ላይ ያካሄደችው ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሊት ከካይሮ እስከ ካርቱም፣ ከጁባ እስከ ቱኒስ፣ ከዲሲ እስከ ኒውዮርክ አጀንዳ ሆኖ ከርሞ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ባጠናቀቀች ማግስት የሦስቱ ሀገራት ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ይሁን የምትለው ኢትዮጵያ ሐሳቧ ሚዛን ደፍቶ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቅቡልነት አገኘ፡፡

የኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ እና ድጋፍ በዚህ ዓመት ከፍ ብሎም ታይቷል፡፡

በመጨረሻም የፌዴራል መንግሥት በሕግ ማስከበር እርምጃው የትግራይ ክልል አርሶአደር የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውንና ሕዝቡም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ ለማድረግ ሰብዓዊነት ያማከለ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወሰነ፡፡ ነገር ግን አሸባሪው ትህነግ በለመደው የጦርነት አባዜው በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ፈጸመ፡፡ በዚህ ጦርነት አሸባሪው ቡድን በማስገደድ ሕፃናትንና አዛውንቶችን አሰልፏል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በአፋር እና በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች በጦርነት ወቅት የሚታፈሩ እና የሚከበሩ ሴቶችን፣ ሕፃናትን እና አረጋውያንን በአጠቃላይ ንፁሃንን የጥቃት ሰለባ አደረጋቸው፡፡ መሰረተ ልማቶች ወደሙ፣ የግል ተቋማት እና የግለሰቦች ሃብት ተዘረፈ፡፡

በተለይም ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም በማይካድራ ከ1 ሺህ 600 በላይ ንጹሃንን የጨፈጨፈው ሽብርተኛው ትህነግ ዛሬም በጭና፣ በአጋምሳ እና ጋሊኮማ ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል፡፡

በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article❝ጦርነቱ ችግርና ፈተና ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን የበለጠ እንደብረት ያጠነከረ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፤ በዚህም የአንድነት መንፈስ ድል እየተመዘገበ ነው ❞ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም
Next articleበድንጋይ ስድስት ክላሽ የማረኩት የድሬ ሮቃው ጀግና።