
በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ የነበረችበትን ፈተና በጀግኖች ቆራጥነት አዲሱን የተስፋ ዓመት እንድትሻገር ስላደረጋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። የዘንድሮው አዲስ ዓመት የማይረሣኝ አከባበር ነውም ብለዋል። ምዕራብ እዝ በትግራይ ክልል መሽገው ክፉ ሃሳብ የነበራቸው ሰዎች እንዲደመሰሱ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል። በቅርቡ በማይጠብሪ ግንባር ያስመዘገቡት ደግሞ ጠላትን ያስደነገጠ ወገንን ያኮራ ነው ብለዋል።
የጠላትን ያልበሰለ የጦርነት ስልትና ፍላጎት ያከሸፈ የጀግንነት ውሎ መሆኑንም ገልፀዋል። ኢትዮጵያን አውቀን አንጨርሳትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀግንነቷ፣ የሀገር ወዳድ ሕዝቦች ሀገር መሆኗን፣ ለመበልፀግ ትልቅ እድል ያላት መሆኗንም አንስተዋል። ጀግናው ሠራዊት ኢትዮጵያን ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንደሚያስቀምጥ ጥርጥር የለኝም ብለዋል።
በጀግንነት መዋጋት ደጋግማችሁ አሳይታችሁናል፣ ጀግንነታችሁን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ተገንዝቧል። አደራ የምላችሁ ከጀግንነት ማግስት ያለን ማንነት ላይ እንድታተኩሩ ነው፣ ማሸነፍ የሚያሰተኛ እንዳይሆንም ነው የገለጹት። ጀግንነታችሁንና አሸናፊነታችሁን በታላቅ ብልሃት እንድትሻገሩት አደራ እላለሁ ነው ያሉት።
በውጊያው ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፣ ጀግና የነበረችው ኢትዮጵያ ናት፣ የእናንተ አንድነት ኢትዮጵያን ያጠነክራል፣ አንድነት ይጠበቅ የጦር ብልሃትና ስልት አይዘንጋ ነው ያሉት።
ዘመናዊ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እየገነባን ነውም ብለዋል። አየር ኃይሉም በከፍተኛ ብቃት እየተገነባ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
የአሁኑ ሽፍታ መለማመጃችን እናደርገዋለን፣ በሽፍታው እየተለማመድን ጠንካራ ተቋም እንገነባለን። ኢትዮጵያን መንካት የማይታሰብ ነው፣ ኢትዮጵያን ከመድፈር ደጋግ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ለሌሎችም ትምህርት እንሰጣለን፣ ኢትዮጵያ እየተዘጋጄች ያለችው ለሰላምና ለብልፅግና ነው፣ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልፅግና ለመድፈር የመጣ ሁሉ ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያዊያን እያሉ ኢትዮጵያ ስለማትሸነፍ በጀግንነት ነፃ ሀገር ተረክበናል በጀግንነት ነፃ ሀገር እናስረክባለን ብለዋል።
የሽፍታው ኃይል ሠራዊቱን ተጠግቶ ውጊያ መምራት አይችልም፣ ጠላቶች ጀግንነት የሚያውቁት ሕፃናትን በማስጨረስ ነው፣ እናንተ ግን ምርኮኞችን ተንከባክባችሁ ስለያዛችሁና የጀግንነትን ጥግ ስላሳያችሁ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያመሰግኗችኋልም ብለዋል። ጀግና ማለት ተዋግቶ መግደል ብቻ ሳይሆን ሲማርክ የሚንከባከብ መሆኑን ስላሳያችሁ ኢትዮጵያ ትኮራባችኋለች ብለዋል።
እናንተ በጦር ግንባር በጀግንነት ያመጣችሁት አሸናፊነት ድሉ በሁሉም ይደገማል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች፣ ነፃነታችን መንካት የሚፈልጉ ሁሉ ይጠፋሉ። የኢትዮጵያ ነፃነት ከልጅ ልጆች የሚተላለፍ የማይሸራረፍ እንደነበረ የሚቀጥል መሆኑን ለዓለም በድጋሜ እናሳያለን ነው ያሉት። የምንፈልገው በሰላም መኖር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልክ እንደ ዓድዋው ሁሉ በአንድነት ድል ለማምጣት እንተጋለንም ብለዋል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ መከላከያ እየገነባን ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሁላችንም ኩራት መሆኗን ተገንዝባችሁ ለዚች ሀገር መድከም መሰዋእት መሆን ክብር ነውም ብለዋል። ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን የምትፈራ፣ ጎረቤቶቿን የምትወድ፣ ተባብራ የምትሰራ ሀገር መሆኗን ለዓለም በድጋሜ እናሳያለንም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ—ከማይጠብሪ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m